የሀገር ውስጥ ዜና

ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመረጃና ደኅንነት አመራር የሰለጠኑ የደቡብ ሱዳን የደህንነት ተቋም አባላትን አስመረቀ  

By Mekoya Hailemariam

February 14, 2022

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመረጃና ደኅንነት አመራር የሰለጠኑ የደቡብ ሱዳን የደህንነት ተቋም አባላትን አስመረቀ  ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከደቡብ ሱዳን አቻው ናሽናል ሴኩሪቲ ሰርቪስ ጋር በጋራ ለመስራት በደረሰው ስምምነት መሰረት ለሀገሪቱ የደኅንነት ተቋም አመራሮች በከፍተኛ የመረጃና ደህንነት አመራር ሙያ ስልጠና በመስጠት አስመርቋል፡፡

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስር በሚገኘው ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ስልጠና የወሰዱት የደቡብ ሱዳን የደኅንነት ተቋም አባላት የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ የተገኙት የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ፥ የሁለቱ ሀገራት የደህንነት ተቋማት በመረጃ ልውውጥ፣ ሽብርተኝነትን በመዋጋት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመቆጣጠር እና ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመከላከል ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የጋራ የደኅንነት ስጋቶችን ለማስወገድ እንዲሁም ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ከቀጣናዊ፣ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ አቻ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ተመስገን፥ የደቡብ ሱዳን ናሽናል ሴኩሪቲ ሰርቪስ አመራሮች በከፍተኛ የመረጃና ደህንነት አመራር ሙያ ስኬታማ በሆነ መንገድ ስልጠናቸውን አጠናቅቀው ለምረቃ መብቃታቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ጠንካራ ትብብር እያደገ መምጣቱን ያሳያል ማለታቸውን አገልግሎቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያደረሰው መረጃ ያመለክታል፡፡

ተመራቂዎቹም በቆይታቸው በመረጃ እና በአመራር ሙያ ያገኙትን እውቀትም ወደ ተግባር በመቀየር ብዙ እንደሚጠበቅባቸው ነው የተናገሩት፡፡

ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁን በምስራቅ አፍሪካ ብሎም በመላው አፍሪካ በመረጃና ደኅንነት ዘርፍ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ያስታወቁት ዳይሬክተር ጀነራሉ፥ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ኦፊሰሮቻቸውን በተቋሙ ለማሰልጠን ፍላጎት እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን ናሽናል ሴኩሪቲ ሰርቪስ ዳይሬክተር ጀነራል ጀነራል አኮል ኮር ኩክ በበኩላቸው ሥልጠናው የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና ላበረከቱት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አመራሮች፣ ለብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ መላው አባላት እና ለሌሎችም የመንግሥት ባለሥልጣናት ላቅ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ካሳ ለምረቃ የበቁት የደቡብ ሱዳን ናሽናል ሴኩሪቲ ሰርቪስ አመራሮች የተጣለባቸውን ከፍተኛ ሃላፊነት መወጣት የሚያስችል በመረጃና ደህንነት ኪነሙያ ያተኮረ ጥልቀት ያለው ስልጠና ማግኘታቸውን አመልክተዋል፡፡