የሀገር ውስጥ ዜና

ድርቁን ለመቀልበስ የሚደርገው ስራ ለአፍታም ስልጣን በተጠሙ አካላት አይሰናከልም – የሶማሌ ክልል መንግስት

By Mekoya Hailemariam

February 13, 2022

አዲስ አበባ፣የካቲት 6፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል መንግስትና ህዝብ ድርቁን ለመቀልበስ የሚያደርጉት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል እንጂ፣ ስልጣን በተጠሙና ለህዝብ ደንታ በሌላቸው ሴረኛ አካላት ለአፍታም አይሰናከልም አለ የክልሉ መንግስት።

የክልሉ መንግስት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ አውጥቷል።

“በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግሥትና ሌሎች የሀገራችን ክልሎች ድርቁን ለመቀልበስ በጋራ ርብርብ በሚያደርጉበት ጊዜ ላለፉት ሶስት አስርተ አመታት በሀገራችን እና በክልላችን የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈፀመው ወንጀለኞች እና ከለውጡ በኋላ በሙስናና ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር በነበራቸው ድብቅ ግንኙነት ከመዋቅር የወጡ ግለሰቦች በውጭና በሀገር ውስጥ ተሰባስበው በሸረቡት ሴራ የክልሉንና የህዝባችንን ሰላም ለማወክ ሙከራ አድርገዋል” ነው ያለው መግለጫው።

የክልሉ መንግስት በመግለጫው “የሶማሌ ክልል መንግሥትና ህዝብ ስልጣን በምርጫ እንጂ በሀይል ለመያዝ የሚደረግ ሙከራ ፈፅሞ አይሳካም” ብሏል።

“ድርቁን ለመቀልበስ የሚደርገው ስራ ለአፍታም ስልጣን በተጠሙ አካላት አይሰናከልም” ይላል መግለጫው።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

የሶማሌ ክልል መንግስትና ህዝብ ድርቁን ለመቀልበስ የሚያደርጉት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል እንጂ፣ ስልጣን በተጠሙና ለህዝብ ደንታ የሌላቸው ሴረኛ አካላት ለአፍታም አይሰናከልም:-

በአሁኑ ወቅት የሶማሌ ክልል ህዝብ የተፈጥሮ የድርቅ አደጋ ገጥሞታል፣ ይህ ድርቅም በመላው የሶማሌ ክልል ህዝብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን አስከትሏል።

ይህ በዝናብ እጥረት ምክንያት የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የሶማሌ ክልል መንግሥት ህዝብና እንሰሳትን ለመታደግ ድርቁ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከ800 ሚልየን ብር በላይ በመመደብ እየሰራ ይገኛል። ከዚህ ጎን ለጎን የተለያዩ አልሚ ምግቦች፣ የእንሰሳት መኖና ውሃን በማድረስና በሽታዎች እንዳይከሰቱ መድሃኒቶችን በማቅረብ የክልሉ መንግሥት ትኩረቱን ሁሉ ድርቁን ለመቀልበስ ላይ ያደረገ ሲሆን በአይነትና በገንዘብ ከተለያዩ ወንድም ክልሎች፣ ግለሰቦችና ድርጅቶች የተገኙ እርዳታዎችም ለህዝቡ ማድረስ ተችሏል።

ይሁን እንጂ ከድርቁ ስፋትና ርዝመት አኳያ ይህ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ለተለያዩ የሀገር ውስጥና አለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ጥሪ አቅርበን ከተለያዩ የሀገራችንና አለም አቀፍ አካላት እርዳታ ተገኝቷል።

ይህ በምስራቅ አፍሪካ የተከሰተው ድርቅ በክልላችን ከተከሰተ ጀምሮ የድርቁን ሁኔታ የሀገራችን ህዝብና ሌሎች አለም አቀፍ አካላት እንዲያውቁት ለማድረግ ለሚዲያ ክፍት አድርገን በርካታ የሀገር ውስጥና አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የድርቁን ሁኔታ በስፋት ዘግበውታል፤ ዘገባዎቹን ተከትሎ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይ የግብረ ሰናይ ድርጅት መሪዎች ወደ ክልላችን በተደጋጋሚ በመምጣት ሁኔታውን በአይናቸው እንዲያዩት ተደርጓል።

የድርቁን ሁኔታ መጥተው ካዩትና ገለፃ ከተደረገላቸው መካከልም የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ክብር ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የኢፌዲሪ ጠ/ሚ ክቡር አብይ አህመድ፣ የተመድ ም/ዋና ፀሃፊ አሚና መሀመድ እና ሌሎች በርካታ አካላት ሲሆኑ፥ ሁሉም የክልሉ መንግሥት እና አመራር ድርቁን ለመቀልበስ እያደረገ ያለውን ርብርብ አድንቀው የበኩላቸውን እንደሚወጡ መናገራቸው ይታወሳል።

የድርቁን አደጋ ለመቋቋም የክልሉ መንግሥት እያደረጋቸው የሚገኙ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መካከል ለአብነት ባለፉት ሳምንት ብቻ 30,000 ኩንታል የተለያዩ አልሚ ምግቦችና የእለት ደራሽ እህሎች ያከተተ ድጋፍ ለ46 ወረዳዎች የደረሰ ሲሆን፥ በድርቅ ከተጠቁ 10 ዞኖች የሚገኙ ከ70,351 አባወራዎች በላይ ተጠቃሚ ሆነዋል።

በተጨማሪም 200 ሚሊዮን ብር የሚገመት የእለት ደራሽ ምግቦች ለ38 ሺህ 978 በላይ አባወራዎችን የተሰራጨ ሲሆን፥ የምግብ እጥረት አደጋን ለመከላከልና ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የተመደበ 70 ሚሊዮን ብር የሚሆን በጀት የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ሊከሰት ይችላል ተብሎ ሪፖርት የተደረገባቸው አካባቢዎች በክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ በኩል ተግባራዊ ተደርጓል።

በሌላ በኩል በ78 ወረዳዎች የሚገኙ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ህዝብን ከተፈጥሮ አደጋው ለመታደግና ተጠቃሚ ለማድረግ መደበኛ ውሃ የማጓጓዝ ስራ በየቀኑ እየተሰራ ሲሆን፥ ከ100 ሺህ በላይ የእንስሳት መኖ ፓኬጆች ወደ 48 ወረዳዎች የተከፋፈሉ ሲሆን፥ ቀደም ሲልም 16 ወረዳዎች 65 ሺህ የመኖ ፓኬጆችን ማድረስ ተችሏል።

በድርቁ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው ፋፋን ዞን የደረሱት ሰዎችና እንስሳትን እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ የተጠናከረ ሲሆን፥ የክልሉን ህዝብ ለተቸገሩ ወገኖቻቸው ያደረጉት ወንድማዊ አቀባበልን የሚመሰገን ነው።

የክልሉ መንግስት ተፈናቃይ ህብረተሰብና ከብቶቻቸው ልዩ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንና በርካታ ተፈናቃዮች የሚገኙበት 63 ቦታዎች አመራሩ በአካል በመሄድ ምግብና መኖን በማድረስ ላይ ናቸው።

በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በተለያዩ የክልሉ አከባቢዎች የሚገኙ 103 የውሃ ጉድጓዶችን እንደአዲስ የተጠገኑ ሲሆን፥ በብልሽት ምክንያት ስራ አቁመው የነበሩት 12 የውሃ ጉድጓዶችም ሲከፈቱ፥ ሌሎች 12 የሚሆኑ አዳዲስ የውሃ ጉድጓዶችንም ተቆፍረው ተግባራዊ ተደርጓል።

እንደ ክልላዊ መንግሥታት በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እየደረሰ ካለው የምግብ፣ የውሃ፣ የመድኃኒትና የእንስሳት መኖ በተጨማሪ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ እንደሚኖሩ የተለዩ አባወራና አቅመደካማ ዜጎች ከተመደበው 529 ሚልየን በ15 ወረዳዎች የሚገኙ ቤተሰቦች እስካሁን 253 ሚሊዮን ብር እንዲከፋፈል መደረጉንም ገልጸዋል።

የተከራችሁ የኢትዮጵያ ህዝቦች በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግሥትና ሌሎች የሀገራችን ክልሎች ድርቁን ለመቀልበስ በጋራ ርብርብ በምናደርግበት ጊዜ ላለፉት ሶስት አስርተ አመታት በሀገራችን እና በክልላችን የተለያዩ የሰበዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈፀመው ወንጀለኞች እና ከለውጡ በኋላ በሙስናና ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር በነበራቸው ድብቅ ግንኙነት ከመዋቅር የወጡ ግለሰቦች በውጭና በሀገር ውስጥ ተሰባስበው በሸረቡት ሴራ የክልሉንና የህዝባችንን ሰላም ለማወክ ሙከራ አድርገዋል።

የእነዚህ ሀይሎች ዋና አላማ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት፣ ክልሉን ለማተራመስና ስልጣንን በሀይል ለመያዝ ሲሆን፣ ህዝባችንን ከድርቁ ለመታደግ ርብርብ በሚናደርግበት ወቅት ለህዝብ ደንታ የሌላቸው እኚህ ሀይሎች ሰላም ለማደፍረስና በድርቅ የተጎዱ ዜጎች እየተደረገ ያለውን እርዳታ ለማሰናከል ያደረጉት ሙከራም ከሽፏል።

የሶማሌ ክልል መንግሥትና ህዝብ ስልጣን በምርጫ እንጂ በሀይል ለመያዝ የሚደረግ ሙከራ ፈፅሞ የሚሳካ እንዳልሆነ ሲገገልፅ፣ ድርቁን ለመቀልበስ የሚያደርገው ስራ ለአፍታም ስልጣን በተጠሙ አካላት አይሰናከልም።

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ህዝቦች በአሁኑ ወቅት የሶማሌ ክልል መንግሥትና ህዝብ ድርቁን ለመቀልበስ እያደረገ ካለው ርብርብ በተጨማሪ ክልሉን የጦር አውድማ ለማድረግና ሰላምን ለማወክ ሴራ እየሸረቡ ከሚገኙ ወንጀለኞች እና በድጋሚ ወደ ስልጣን ለመመለስ በህገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር በመታገል ላይ ሲሆን፥ ይህንን በጋራ ለመመከት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ እናቀርባለን።

የተከበራችሁ ደከመን ሰለቸን ሳትሉ የህዝብን ሰላም ሌተ ቀን የሚትጠብቁ የፀጥታ ሀይሎቻችን፣ በእናንተ ጥረትና ብርታት የተረጋገጠው የክልላችን ሰላምና ፀጥታ እንደ ከዚህ ቀደም ሁሉ በአሁኑ ወቅት ሰላም ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ለህግ በማቅረብ በድጋሚ አለኝታነታቹን እንድታረጋግጡ ጥሪ እናቀርባለን።

የተከበራችሁ የሀገራችን ሚዲያዎች በአሁኑ ወቅት ይህን የተፈጥሮ ድርቅን ለአለም ለማድረስ እያደረጋችሁ ያላችሁትን ጥረት የምናደንቅ ሲሆን፥ የክልሉን ሰላም ለማወክና ስልጣንን በሀይል ለመያዝ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ አካላት የሚያናፍሱት የሀሰት ወሬ እንድትታገሉ ጥሪ እናቀርባለን።

የተከበራችሁ የሀገራችን ባለሀብቶች፣ የዲያስፖራና የንግዱ ማህበረሰብ፣ ግብረሰናይ ድርጅቶች፣ አቅምና ሀብቱ ያላችሁ ወገኖች ዛሬ ላይ የሶማሌ ክልል ህዝብ በድርቅ እየተፈተነ ይገኛል፣ ስለሆነም ባላችሁ አቅም ሁሉ ከደጉ የሶማሌ ክልል ህዝብ ጎን ትሆኑ ዘንድ በድጋሚ ጥሪ እናቀርባለን።

በመጨረሻም ይህ የተፈጥሮ የድርቅ አደጋ ለመቀልበስ ሁሉም ሰብአዊነት የሚሰማቸው ዜጎች ጋር በጋራ እንደምንሰራ እየገለፅን፣ ለፖለቲካ አጀንዳቸው ብለው ድርቁን ለፖለቲካ መጠቀሚያ የሚያደረጉት ሴረኞች የሶማሌ ክልል መንግሥት እንደማይታገስ እናሳስባለን።

•ሰላማችንን እንጠብቅ •በድርቁ የተጎዱ ዜጎችቻችንን እንርዳ •ፈተናዎችን በጋራ እንለፍ

የሶማሌ ክልል መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ የካቲት 6/ 2014 ዓ. ም ጅግጅጋ