Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የደቡብ አፍሪካ በሚሊየን የሚቆጠሩ የውጭ ዜጎች ከሀገሪቱ እንዲወጡ የሚያደርገውን የቪዛ ህግ አፀደቀች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በሃገሪቱ በክህሎት ላይ ብቻ የተመሰረተ የስራ ቪዛ እንዲሰጥ የሚያዘውን ህግ አፀደቁ።
ሀገሪቱ የኢሚግሬሽን ሕጎቿን እያጠናከረች ሲሆን፥ ፕሬዚዳንቱ የተሻሻለውን የወሳኝ ክህሎት የስራ ቪዛ ማፅደቃቸው በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኙ በሚሊየን የሚቆጠሩ የውጭ ሀገራት ሰራተኞችን ሀገሪቱን እንዲለቁ ያደርጋል ነው የተባለው፡፡
በተለይም በውጭ አገር ዜጎች የተያዙት አስተናጋጅነት፣ አነስተኛ ንግዶችን ማስኬድ፣ የሱቅ ንግድ እና በጤና እና ውበት ኢንዱስትሪ ውስጥ መስራትን ጨምሮ አንዳንድ ስራዎች አሁን ለደቡብ አፍሪካ ዜጎች ብቻ የተተዉ ይሆናሉ ተብሏል።
ወደ 3 ሚሊዮን የሚገመቱ የውጭ ሀገር ዜጎች በደቡብ አፍሪካ ያለ በቂ ሰነድ በህገ ወጥ መንገድ እየሰሩ ነው የተባለ ሲሆን፥ ይህም ከስራ ገበያ እየተገፉ እንደሆነ የሚሰማቸውን የሃገሪቱ ነዋሪዎች አስቆጥቷል።
በአሁኑ ጊዜ በቀድሞ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ማቩሶ ምሲማንግ የሚመራው የስራ ቪዛ ስርዓት አጠቃላይ ግምገማ በመካሄድ ላይ ነው ተብሏል።
በዚህ አዲስ የቪዛ ህግ 200 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች በደቡብ አፍሪካ ባላት ዚምባብዌ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚኖረው ተመልክቷል።
በፀደቀው አዲስ የቪዛ ህግ መሰረት በሀገሪቱ መቆየት የማይችሉ የውጭ ሀገራት ዜጎች እስከያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት 2022 መጨረሻ ድረስ ሀገሪቱን ለቀው መውጣት እንደሚጠበቅባቸው ኒውስ 24 ዘግቧል።
Exit mobile version