Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አካታች ብሔራዊ ምክክሩን ከማሳካት አንፃር የምሁራንን ሚና የሚዳስስ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “አካታች ብሔራዊ ምክክሩን ከማሳካት አንፃር የምሁራን ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ የሠላም ሚኒስቴር ከባህርዳር ዩኒቨርሺቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በባህርዳር እየተካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ የሠላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለምን ጨምሮ ሚኒስትር ድኤታ ታየ ደንደአ ፣የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን እና ስትራቴጅ ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዘውዱ እምሩን እና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሠብ እየተሳተፉ መሆኑ ተገልጿል።

እንደ ሀገር በሠለጠነ መንገድ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ መሻገርን መለማመድ እና ለትውልድም ማሻገር ይገባል ያሉት የሠላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም÷ የዜጎች ደህንነት የተረጋገጠበት፣ ሠላም የሠፈነበት እና የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲመሠረት የጋራ መግበባት ላይ መድረስ ይገባል ብለዋል፡፡

ለትውልዱ አዲስ ምዕረፍ መክፈት ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ÷ ከጥላቻ ፍረጃና የተዛቡ ትርክቶች ወጥተን በሠለጠነ መንገድ መወያየት፣ ሀሳብና ልዩነትን ማክበር የሚቻልበት ሀገር እንዲሆን የተግባር ስራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

ምሁራን ለዚህ ስኬት ሚናቸው የጎላ መሆኑም የተገለጸ ሲሆን÷ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን እና ስትራቴጅ ኮሚዩኒኬሽን ም/ፕሬዚዳንት ዶክተር ዘውዱ እምሩ በበኩላቸው÷ ዩኒቨርሲቲዎች ችግሮችን በአመክንዮና ውጤት የሚመሩ ምሁራን የሚገኝባቸው እና የሚፈራባቸው በመሆኑ በሠላም ግንባታ እና እንደ ሀገር የተወጠነው ምክክር ውጤታማ እንዲሆን ከዚህ ተቋም ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።

ምክክሩን ገለልተኛ የህዝብ ምርጫ የሆኑ ግለሠቦች የሚመሩት መሆኑንም ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

መንግስት፣ ምሁራን፣ ሲቪክ ማህበራት እና መላ ህብረተሠቡ የጋር ርብርብ በማድረግ ይህን አዲስ ምዕራፍ ስኬታማነት በቅንነት ለውጤት ሊሠሩ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version