አዲስ አበባ፣የካቲት 4፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ወይም ‘ዶፒንግ’ የሚመለከቱ ጉዳዮች በመደበኛ ትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ተካትተው ከ5ኛ ክፍል ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተመላከተ፡፡
የኢትዮጵያ የፀረ- አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ዋና ዳይሬከተር አቶ መኮነንን ይደርሳል የስፖርት አበረታች ቅመሞችን የሚመለከቱ ጉዳዮች በመደበኛ ትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ተካትተው ከ5ኛ ክፍል ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የስፖርት አበረታች ቅመሞችን የሚመለከቱ ጉዳዮች በመደበኛ ትምህርት ካሪኩለም ውስጥ መካተቱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ከማምጣቱም በላይ ከስፖርት አበረታች ቅመሞች ነፃ የሆኑ ጤናማ ስፖርተኞችና ንፁህ ስፖርት ለማስፋፋት የሚረዳ መሆኑንም ዋና ዳይሬከተሩ ገልጸዋል።
ከስፖርት አበረታች ቅመሞች ነፃ የሆኑ ጤናማ ስፖርተኞች ተፈጥረውና ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ ተወዳድሮ ማሸነፍ ባህል ለማድረግና ዶፒንግን በየደረጃው ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባለስልጣኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን የሚመለከቱ ጉዳዮች በክለቦች፣ በብሔራዊ ቡድንና በስፖርት የማሰልጠኛ ማዕከላት መደበኛ የስፖርት ስልጠና ካሪኩለም ውስጥ ተካትተው ከስፖርቱ ጎን ለጎን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለተተኪ ስፖርተኞች ስልጠናው እንዲሰጥ ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቶት በመሰራት ላይ እደሚገኙ ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡