የሀገር ውስጥ ዜና

ማንኛውም ሰው ፈቃድ ሳይወስድ የበጎ አድራጎት ኮሚቴ በማቋቋም ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ እንዳይሰራ ተከለከለ

By Alemayehu Geremew

February 10, 2022

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ማንኛውም ሰው ፈቃድ ሳይወስድ የበጎ አድራጎት ኮሚቴ በማቋቋም ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ እንዳይሰራ መከልከሉን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አስታወቀ።

ከዚህ ቀደም ፈቃድ ሳይኖራቸው የበጎ አድራጎት ኮሚቴ አቋቁመው፣ በገንዘብ ማሰባሰብ ላይ የሚገኙ ግለሰቦችና ቡድኖች ከባለስልጣኑ ፈቃድ በመውሰድ ወደ ህጋዊ አሰራር መግባት እንዳለባቸውም አሳስቧል።

ይህንን ተግባራዊ በማያደርጉ አካላት ላይ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ አስፈላጊውን ርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቁን ኢዜአ ዘግቧል።

ከባለስልጣኑ ፈቃድ ሳይኖራቸው በህዝብ ስም በማንኛውም መንገድ ገንዘብ የማሰባሰብ ስራዎችን መስራት የተከለከለ መሆኑን የገለጸው ባለስልጣኑ÷ በህዝብ ስም የሚሰበሰብ ገንዘብ በህገ ወጥ መንገድ እንዳይባክን የመከላከልና የመጠበቅ ስልጣን እንዳለው አመልክቷል።