Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሀገራዊ ጥሪን ተቀብለው በሁሉም አውደ-ግንባሮች ሚናቸውን ለተወጡ አካላት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ምስጋና አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ ጥሪን ተቀብለው ህይወታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ሃብታቸውን፣ እውቀታቸውንና ጊዜያቸውን በመስጠት በሁሉም አውደ-ግንባሮች ሚናቸውን ለተወጡ አካላት የአዲስ አበባ አስተዳደርከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ምስጋና አቀረቡ።

ከንቲባዋ የአዲስ አበባ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በደጀንም በግንባርም ከፊት ሆነው በጀግንነት ለመሩት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ለጦር አመራሮች፣ ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት አባላትና ለፌደራልና ለክልል ፀጥታ ሀይሎች እንዲሁም ለአማራና ለአፋር ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡


በግማሽ ዓመቱ በተከናወነው ተግባር ለ297 ሺህ 696 ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉንም ገልጸዋል።

በ “በቃ” ዘመቻ የኢትዮጵያን አንድነት አንግበው ድምፃቸውን ለዓለም ላሰሙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች እና ለመላው ሰላም ወዳድ ወገኖችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

“ሀገራዊ ጥሪውን ተቀብላችሁ ህይወታችሁን፣ ጉልበታችሁን፣ ሃብታችሁን፣ እውቀታችሁንና ጊዜያችሁን በመስጠት በሁሉም አውደ-ግንባሮች ሚናችሁን ለተወጣችሁ ሁሉ፥ ለሠራችሁት አኩሪ ታሪክ ከልብ የመነጨ አድናቆትና ልባዊ ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን” ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ከንቲባዋ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት÷ 24 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች በህልውና ዘመቻው መሳተፋቸውን ፣400 የጤና ባለሙያዎች ወደ ጦር ግንባር በማምራት ሙያዊ ሀላፊነታቸውን መወጣታቸውን እና 18 የጤና ተቋማትን መልሶ በማቋቋም የተለያዩ የህክምና መድሃኒቶችና መሳሪያዎች ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የአስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ተግባራት እንደገና ለመወሰን የከተማ አስተዳደሩ ባካሄደው የመዋቅር ማሻሻያ ጥናት አዋጅ ቁጥር 74/2014 በዚሁ ምክር ቤት ፀድቆ 71 የነበሩትን የመንግስት ተቋማት ወደ 46 በመቀነስ መልሶ የማደራጀት ስራ ተሰርቷልም ነው ያሉት፡፡

በግማሽ አመቱ ለ227 ሺህ 500 ስራ ፈላጊዎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ297 ሺህ 696 ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉንም ገልጸዋል።

ለ1 ሺህ 514 ኢንተርፕራይዞች የካፒታል አቅማቸውን ለማሳደግ ከ449 ሚሊየን ብር ብድር ለመስጠት ታቅዶ 269 ሚሊየን 247 ሺህ ብር ብድር መሰጠቱን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version