Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አንጎላ በሠላም ማስከበር ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራትና ልምድ ለመቅሰም ፍላጎት እንዳላት ገለጸች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የአንጎላ አምባሳደር ፍራንሲስኮ ጆሴ ዳክሩዝ፥ ሀገራቸው በሠላም ማስከበር ዘርፍ ከኢትዮጵያ የካበተ ልምድና ተሞክሮ መቅሰም እንደምትፈልግና በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት ገለጹ።
ኢትዮጵያና አንጎላ ለረዥም ዘመናት የቆየ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ሀገሮች መሆናቸውን አምባሳደሩ አንስተው፥ ይህም የሀገራቱን ሁለንተናዊ ትብብር የሚያጠናክር እንደሆነ ገልጸዋል።
የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን ሊያጠናክር በሚያስችል መልኩ በቀጣይም በጋራ ሊሰሩ በሚያስችሉ መስኮች ላይ በትብብር ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸውም አምባሳደሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና አንጎላ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1979 መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1950 እስከ 1953 ከተካሄደው የኮርያ ጦርነት ጀምሮ እስካሁን በተለያዩ የሠላም ማስከበር ዘመቻዎች ላይ እየተሳተፈች ተልዕኮዋን በብቃት እየፈጸመች ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ግጭት ለማብረድና ሠላም ለማስፈን በኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳንንና ደቡብ ሱዳንን በሚያወዛግበው የአብዬ ግዛት እንዲሁም በዳርፉርና በቀጣናው ተሳታፊ መሆኗም ይታወሳል፡፡
አሁንም ኢትዮጵያ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር የተሰማራውን የሠላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ለማገዝ ሰራዊት በመላክ እየተሳተፈች እንደምትገኝ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version