Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኮምቦልቻ ሆስፒታል ወደ አገልግሎት መመለሱ ለተገልጋዮች እፎይታን ፈጥሯል – ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦርነት ምክንያት ንብረቶቹ የወደሙበትና የተዘረፉበት የኮምቦልቻ አጠቃላይ ሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ለተገልጋዮች እፎይታ እንደፈጠረላቸው ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በጦርነቱ ወቅት ከፍተኛ ጉዳት ያስተናገደውና ንብረቶቹን ያጣው ሆስፒታሉ በተለይ የአለርት ሆስፒታል ባደረገለት የሕክምና ማሽኖች እና የባለሙያ ድጋፍ የማዋለድ፣ የተመላላሽ፣ የጨቅላ ህፃናት፣ የድንገተኛ እና የመሳሰሉትን የሕክምና አገልግሎቶች መጀመሩ ለኅብረተሰቡ እፎይታን ፈጥሯል ሲሉ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ተፈራ ጎበዜ ገልጸዋል፡፡
ሆስፒታሉ ሥራ በጀመረ በአንድ ወር ውስጥ ከ500 በላይ ተመላላሽ ታካሚዎችን ማስተናገዱን የገለፁት ዶክተር ተፈራ ÷ በአጠቃላይ በሕፃናት፣ በሥነ አዕምሮ፣ በዓይንና ጥርስ፣ በድንገተኛ ፣ በማዋለድና በተኝቶ ሕክምናዎች ከ1 ሺህ በላይ ተገልጋዮችን ማስተናገዱን ጠቅሰዋል።
ሆስፒታሉ ባለፈው ዓመት ሥራ መጀመሩንና የተሟላ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ያስታወሱት የሆስፒታሉ ሜትረን ወንድወሰን መኮንን ÷ በጤና ሚኒስቴር እና በክልሉ ጤና ቢሮ አስተባባሪነት እንደ አለርት ሆስፒታል እና ቀይ መስቀል የመሳሰሉ ተቋማት ባደረጉላቸው ድጋፍ ወደ ሥራ መመለሳቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል እና ሰራተኞች በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰበት የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ቀበሌ 03 ጤና ጣቢያ 1 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ጤና ጽህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ አቶ ወገኔ በላይ፥ የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል እና ሰራተኞች በጦርነቱ የወደሙትን ንብረቶች ለመተካት ያደረጋችሁት ድጋፍ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ መልዕክት አለው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ሁለት ዶክተሮች፣ አንድ ነርስ አዋላጅና አንድ የፋርማሲ ባለሙያ በኮምቦልቻ ከተማ ቀበሌ 03 ጤና ጣቢያ ለተወሰኑ ቀናት የነፃ ህክምና አገልግሎት እንደሚሰጡ የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ አንዷአለም መንግስቱ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version