Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባት ለማምረት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ከሚሰሩ ሥራዎች ጎን ለጎን በአሁኑ ወቅት ጤና ሚኒስቴር ከአፍሪካ ኅብረት፣ የበሽታዎች መከላከል ማዕከል እና ከአጋር ጅርጅቶች ጋር በመሆን የኮቪድ-19 ክትባት ማምረት የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡
ዶክተር ሊያ ከአፍሪካ ሀገራት የኮቪድ-19 ክትባት በማምረት ደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው ÷ የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራቱ ክትባቱን በየግላቸው ከማምረት ይልቅ እንደ አህጉር በጋራ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
ክትባቱን የማምረት እንቅስቃሴ እንደ ሀገር እና አህጉር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ታምኖበት ኢትዮጵያ በንቃት እየተሳተፈች መሆኗን ዶክተር ሊያ ተናግረዋል፡፡
ክትባቱም በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል የገበያ አዋጭነት ጥናት፣ ከአጋር አገራት እና ድርጅቶች ጋር ውይይትና ልምድ ልውውጥ ማድረግ እንዲሁም ምርቱን ለማስጀመር የሚያስችሉ ተግባራትን በዝርዝር የመለየት ሥራ መሠራቱን ለኢፕድ ገልጸዋል፡፡
ዝርዝር ጥናቶች ሲጠናቀቁ ሀገሪቷ ክትባቱን ወደ ማምረት እንደምትገባም ነው ያስታወቁት፡፡
ወረርሽኙ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በጤናው ሴክተር ላይ በርካታ ጫናዎች ቢከሰቱም÷ በተከታታይ በተሰሩት ሥራዎች ያጋጠሙትን አሉታዊ ተጽእኖዎች ለመቀነስ እና የሀገሪቷን የጤና ሥርዓት ለማሻሻል ተችሏል ብለዋል ሚኒስትሯ።
የጤና ተቋማትን በተገቢው ሁኔታ እንዲደራጁ፣ የጤና ስርዓቱ እንዲስተካከል፣ የላብራቶሪ የመመርመር አቅም እንዲጠናከር፣ የጽኑ ህሙማን ህክምና እንዲሻሻል እና ኦክስጅንም የማምረት አቅም እንዲጠናከር የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል።
የፋርማሲ መገልገያ ቁሳቁሶች በተለይም ሳኒታይዘር፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች፣ የእጅ ጓንቶች፣ ተጓዳኝ የመከላከያ መሳሪዎች እና የመሳሰሉት በአገር ውስጥ ማምረት የሚያስችል አቅም ማጎልበት ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version