የሀገር ውስጥ ዜና

ጠ/ሚ ዐቢይ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም እና በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽዖ ላበረከቱ  ሁሉ ምስጋና  አቀረቡ

By Feven Bishaw

February 06, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም እና በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ሁሉ  ምስጋና  አቅርበዋል፡፡

 

የህብረቱን ጉባዔ  አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማህበራዊ ትሥሥር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በመዲናችን አዲስ አበባ እንዲደረግ የአባል ሀገራት መሪዎች መወሰናቸውን ተከትሎ ወንድማዊ አጋርነት የታየበት የኅብረቱ ጉባኤ በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት ተካሂዶ በስኬት መጠነቀቁን ገልጸዋል።

 

“ጉባኤውን በንቃት የመሩትን የኅብረቱን ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ጨምሮ ለጉባኤው ስኬት አስተዋጽዖ ያበረከቱ አካላትን ኢትዮጵያ  ታመሰግናለች”  ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በምስጋና በመልዕክታቸው።

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያስተላለፉት ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

 

የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም እና በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽዖ ላበረከታችሁ ምስጋና ይድረስ!

 

የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በመዲናችን አዲስ አበባ እንዲደረግ የአባል ሀገራት መሪዎች መወሰናቸውን ተከትሎ ወንድማዊ አጋርነት የታየበት የኅብረቱ ጉባኤ በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት ተካሂዶ በስኬት ተጠናቅቋል።

የኅብረቱ ጉባኤ ፍሬያማ ውይይት የተካሄደበት፣ ለአህጉራችን የሚጠቅሙ ውሳኔዎች የተላለፉበት፣ ከምንም በላይ ወንድማዊ አጋርነት የታየበት ነበር ማለት ይቻላል።