Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሺ ጂንፒንግ ለ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

 አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይናው ፕሬዚደንት ሺ ጂንፒንግ ለአፍሪካ ህብረት 35ኛው የመሪዎች ጉባኤ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
 
ፕሬዚደንቱ ባስተላለፉት መልዕክት ህብረቱ ከተመሰረተ 20 ዓመት እንደሞላው አስታውሰው፤በእነዚህ ዓመታትም በህብረት በመቆም በአፍሪካ ልማት እንዲረጋገጥ፣አህጉራዊ ትስስርን በማጠናከር እና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ቁርጠኝነቱን ማሳየቱን ገልጸዋል።
 
ይሄ ቁርጠኝነት በአህጉሩ ሰላም፣መረጋጋት፣ልማት እና አፍሪካ በዓለም አደባባይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆና እንድትወጣ የሚያደርጉ ስራዎችን በመስራት ጭምር ሊረጋገጥ ይገባልም ብለዋል፡፡
 
ፕሬዝዳንት ሺ እኤአ 2021 የቻይና አፍሪካ ግንኙነት ዳብሮ የታየበት ዓመት እንደነበር አስታውሰው፤ህዳር ወር ላይ 8ኛው የቻይና አፍሪካ የሚኒስትሮች ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ መካሄዱንና በዚህም በመጪዎቹ 3 ዓመታት በቻይና-አፍሪካ በትብብር የሚተገበሩ 9 ፕሮግራሞች ተቀርጸው ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡
 
እነዚህ ፕሮግራሞች ቻይና እና አፍሪካ ለያዙት የቻይና-አፍሪካ የጋራ ማህበረሰብ የመፍጠር ራዕይ መሳካት ሚናው ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
 
ቻይና በጋራ የሚኒስትሮቹ ጉባኤ የተቀረጹትን ፕሮግራሞች ከአፍሪካዊያን ጋር ለመተግበር መዘጋጀቷን መግለጻቸው ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
የአንድ መንገድ አንድ ቀበቶ የትብብር ተነሳሽነት እና የአፍሪካ ህብረት የ2063 የልማት ግብን ለማሳካት በጋራ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
 
ፕሬዚዳንቱ አክለውም የአፍሪካ አህጉር ነጻ የንግድ ቀጠና ስርዓት በመዘርጋትም የቻይና አፍሪካ ትብብር ማዕቀፍን ከፍተኛ የጥራት እና የልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የቻይና-አፍሪካ የወዳጅነት እና የትብብር ማዕቀፉን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
Exit mobile version