የሀገር ውስጥ ዜና

በቱሪዝሙ መስክ እንደአህጉር የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ አፍሪካውያን በአንድነት ልንቆም ያስፈልጋል – ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

By Meseret Awoke

February 05, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ በቱሪዝሙ ዘርፍ እንደአህጉር ያጠላበትን ጥላ ለመሻገር አፍሪካውያን በአንድነት መቆም እና መደጋገፍ ያስፈልገናል ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ገለጹ፡፡

የአፍሪካ ህብረት ጉባዔን ምክንያት በማድረግ ለመሪዎች የተዘጋጀ የእራት ግብዣ መርሃ ግብር በወዳጅነት ፓርክ እየተካሄደ ነው፡፡

በመርሃ ግብሩ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ፥ በ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለተሳተፉ እንግዶች እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል፡፡

የዛሬው ምሽት የአንድነት እና የወዳጅነት ብሩህ ተስፋን ለምንፈልጋት አፍሪካ ለመስጠት ቃል ያሰርንበት ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ እና ሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተገነቡ የሚገኙ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን አንስተው ማብራሪያ ሰጥተውበታል፡፡

የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባን እንደስሟ ለመሆን ባለፉት ሶስት ዓመታት እያሳየች ያለውን ለውጦች አንስተዋል፡፡

አብዛኛው የአፍሪካ የቱሪዝም ዘርፍ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመከሰቱ ምክንያት ክፉኛ መጎዳቱን አንስተው ፥ ዘርፉን ከእንደዚህ ዓይነት አደጋዎች ለመከላከል የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት፡፡

እንደአብነትም የአፍሪካ አገራት የእርስ በርስ የባህል መጋራት፣ መግባባት እና መደጋገፍ መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያስችል ነው በዋነኝነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!