Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አቶ ደመቀ መኮንን የአቶሚክ ኃይልን ለልማት ለመጠቀም ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ትብብር እና ድጋፍ እንዲያደርግ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን ራፋኤል ማሪያኖ በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ደመቀ መኮንን ፥ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ለዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባን በስኬት በማስተናገድ ላይ እንደምትገኝ ጠቅሰው ፥ ይህም በኢትዮጵያ ያለውን ሠላም አመላካች መሆኑን አንስተዋል።

አቶ ደመቀ የአቶሚክ ኃይልን ለልማት ለመጠቀም በተለይም በግብርና ልማት ዘርፍ ካለው ጠቀሜታ አንጻር በኢትየጵያ በኩል በዘርፉ ያለውን ትብብር ለማጠናከር ፍላጎት ያለ መሆኑን ጠቅሰው ፥ የኤጀንሲውን ድጋፍ ጠይቀዋል።

አክለውም ፥ ኤጀንሲው ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖረውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ይረዳ ዘንድም በሀገራችን ማዕከል እንዲያቋቁም በኢትዮጵያ በኩል ፍላጎት ያለ መሆኑንም ገልጸውላቸዋል።

ራፋኤል ማሪያኖ በበኩላቸው ÷ በዛሬው ቀን ተከብሮ የሚውለውን የዓለም አቀፍ የካንሰር ቀን አንስተው ፥ ካንሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያደርሰውን ከፍተኛ የጤና ጉዳት ጠቅሰዋል፡፡

ኤጀንሲያቸው በኢትዮጵያ የካንሰር ሕክምና ማዕከል የማቋቋም ዕቅድ እንዳለው ገልጸዋል።

ከኢትየጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች ለመተባበር ኤጀንሲያቸው ዝግጁ መሆኑንም ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

Exit mobile version