የሀገር ውስጥ ዜና

በአሸባሪው የህወሓት ቡድን እጇን በጥይት ተመትታ የተጎዳችው ተማሪ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እየወሰደች ነው

By Alemayehu Geremew

February 03, 2022

አዲሰ አበባ፣ጥር 26፣2014 (ኤፍ ቢሲ) አሸባሪዉ የህወሓት ቡድን በከፈተው ጦርነት እጇን በጥይት ተመታ ጉዳት የደረሰባት ተማሪ ቃልኪዳን ተኮላ ከህመሟ ሳታገግም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና እየወሰደች ነው።

ተማሪ ቃልኪዳን ተኮላ ÷ የኮምቦልቻ መሰናዶ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ስትሆን ጉዳት የደረሰባት ህዳር 16 ቀን 2014 ነበር።

ተማሪዋ ግራ እጇን በጥይት የተመታች ቢሆንም የቀኝ እጅ ነርቯም ስለተጎዳ ቀኝ እጇ እንደማይፅፍላት ለትምህርት ቤቱ በማመልከቷ ፈተናውን እያነበበችና በሰዎች ድጋፍ እየፃፉላት ፈተናውን በመውሰድ ላይ ትገኛለች፡፡

ተማሪ ቃል ኪዳን ÷ መምህራኖቿ “ከሕመምሽ አገግመሽ ሠኔ ላይ ትፈተኛለሽ” ቢሏትም “ወደፊት የእጄ ሁኔታ አይታወቅም፣ ቀዶ ጥገናም ሊያስፈልገኝ ይችላል፣ብዙ ጊዜ ከምጠብቅ ሕመሜን ችዬ ብፈተንና ሕክምናው ላይ ባተኩር ይሻላል” በሚል ፈተናውን መውሰዷን አስረድታለች።

ተማሪዋ አባቷ በሕይወት እንደሌሉና ከአቅመ ደካማ እናቷ ጋር እንደምትኖር የሕክምና አገልግሎት ለማግኘትም አቅም እንደሌላት ገልጻ ድጋፍ እንዲደረግላትም ጠይቃለች።

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር በቀለ ወርቁ ÷ በጦርነቱ ምክንያት ሁለቱ እጆቿ ላይ ጉዳት የደረሰባት ተማሪ ቃል ኪዳን ተኮላ ትምህርት ቤቱ ፈታኝ በመመደብ ፈተናውን እንድትወስድ ማድረጋቸዉን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።