Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሚኒስቴሩ የነዳጅ ማደያዎችን አስጠነቀቀ፤ የየካቲት ወር ዋጋም ባለበት እንደሚቀጥል ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አንዳንድ ኩባንያዎችና የነዳጅ ማደያዎች ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር እያደረጉ ካለው ህገወጥ እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ አሳሰበ፡፡
የንግድ ስርዓቱን ለማዛባት ያልተገባና ህገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው በሚገኙ ኩባንያዎችና ማደያዎች ላይ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አሳውቋል፡፡
በሌላ በኩል ሚኒስቴሩ ከጥር 26/2014 ዓ.ም እስከ የካቲት 30/2014 ዓ.ም ድረስ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር ሲሸጥበት በነበረው ዋጋ እንዲሸጥ ወስኗል፡፡
ነባራዊ የዓለም የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ በመጨመር ላይ ቢሆንም ውሳኔው የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥሉ ለማስቻል መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የነዳጅ ስርጭት እና አቅርቦቱ ላይ ምንም አይነት ችግር የለም ሲል አስታውቋል።
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ሀይለማሪያም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥‘’ነዳጅ የለም’’ በሚል እየተናፈሰ ባለው ወሬ ተሽከርካሪዎች በማደያዎች ነዳጅ ለመቅዳት የሚያደርጉት ረዣዥም ሰልፎች ከእውነታው ጋር የተቃረነ ተግባር ነው።
አለ የሚባለው ችግር ለእኛም ግልጽ አይደለም ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ፥ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የነዳጅ ስርጭት ጊዜውን ጠብቆ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለአለብነትም ጥር 19 ቀን 2014 ዓ.ም በየቀኑ በአማካይ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ የተሰራጨ ሲሆን ፥ ትናንትና ብቻ 3 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ ወደ ገበያ መሰራጨቱን አንስተዋል።
ሆኖም በየወሩ መጨረሻ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ጋር ተያይዞ ‘‘የዋጋ ልዩነት ይኖራል’’ በሚል ተሽከርካሪዎች በማደያዎች መሰለፋቸው ከዚህ ቀደም ከሚፈጠረው ሁኔታ መገመት ይቻላልም ነው ያሉት።
አንዳንድ አሽከርካሪዎችም በነዳጅ ማደያዎች ተሸከርካሪዎች በመሰለፋቸው ብቻ ነዳጅ የሌለ መስሏቸው የሚሰለፉ እንዳሉም ነው የጠቀሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለስርጭት እየቀረበ ያለው ነዳጅ በመጠኑ እየጨመረ ከመምጣት ውጪ ቅናሽ የታየበት አይደለም ያሉት አቶ ታደሰ ፥ በመሆኑም ህብረተሰቡ በሚናፈሱ ወሬዎች ሊታለል አይገባም ብለዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version