የሀገር ውስጥ ዜና

ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በቱሪዝም ዘርፍ የተደረጉት ቅድመ ዝግጅቶች አበረታች መሆናቸው ተገለጸ

By Meseret Awoke

February 02, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን አስመለክቶ በቱሪዝም ዘርፍ የተደረጉት ቅድመ ዝግጅቶች አበረታች መሆናቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር አማካሪ አቶ ጌትነት ይግዛው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ከምትሆንባቸው የቱሪዝም ዘርፎች አንዱ የኮንፈረንስ ቱሪዝም መሆኑን ጠቅስዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት የመሪዎችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ ተከትሎ ኢትዮጵያ ከኮንፈረንስ ቱሪዝም ተጠቃሚ እንድትሆን በሆቴሎች እና በመዲናዋ በሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች እየተደረጉ ያሉት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በጉባኤው የተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና ልዑካን ቡድኖች የሚመጡ በመሆኑ እንገዶቹ የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ እና በቆይታቸውም ጥሩ ትውስታ ይዘው እንዲሄዱ ለማድረግ ተጨማሪ ዝግጅቶችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው አማካሪው የጠቆሙት፡፡

በተለይም እንግዶች በቆይታቸው ጥሩ እና ሰላማዊ ጊዜ እንዲያሳልፉ ለማድረግ የሰላምና ፀጥታ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል ፡፡

ኢትዮጵያ በባህል እና ቅርስ ቱሪዝም የምትታወቅ መሆኑን ያነሱት አማካሪው ÷ በአዲስ አበባ የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎች እየተስፋፉ መሆኑን ተከትሎ ሀገሪቱ ከኮንፈረንስ ቱሪዝም ገቢ የማግኘት አቅም እንዳላት አመላክተዋል፡፡

ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በመዲናዋ የሚካሄዱ ኮንፈረንሶችን ወደ ክልል ከተሞች በማስፋፋት ከኮንፈረንስ ቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት የደበዘዘውን የኢትዮጵያ መልካም ገፅታ ለማደስ በአዲስ አበባ የሚካሄደው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ጥሩ አጋጣሚ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ የኢትዮጵያን በጎ ገፅታ ለመገንባት መረባረብ እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!