አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ህብረቱ የአፍሪካን የግብርና ዘርፍ ለማጠናከር ያወጣውን ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም በሚመለከት ለመሪዎች ጉባኤ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ በመግለጫቸው÷የሕብረቱ የሥራ አስፈጻሚዎች ጉባኤ ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ገልጸው፥ የህብረቱ የመሪዎች 35ኛ ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ ረቂቅ አጀንዳዎችን እንደሚያዘጋጅና በመሪዎች ውይይት እንደሚደረግበት ጠቁመዋል፡፡
የስራ አስፈጻሚዎችን ውይይት መጠናቀቅ ተከትሎም የፊታችን ቅዳሜና እሁድ የመሪዎች ጉባኤ እንደሚካሄድ ነው የገለጹት፡፡
በአፍሪካ የስርዓተ ምግብ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተለይ ጠንካራ የግብርና ዘርፍ ስለመመስረት፤ የሰው ሃብት ልማትን ማጠናከርና መጠቀም እንዲሁም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎችን ማፋጠን አስፈላጊነት ላይ ጉባኤው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚመክር ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል ከበርካታ ጫናዎች በኋላ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና 40ኛው የሕብረቱ የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጉባኤ በአዲስ አበባ ለመካሄድ መብቃቱ በርካታ ፋይዳዎች እንዳሉት ጠቁመው÷ ብዙ ሀገራት ዜጎቻቸውንና ሌሎች ዜጎችን ከኢትዮጵያ እንዲወጡ በሚወተውቱበት ጊዜ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ዜጎቻቸው እዚሁ እንዲቆዩ በማድረግ ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸውን ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ለዚህም ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፥ ይህም ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ጉባኤውን ለማዘጋጀት በርካታ ዝግጅቶችን ስታደርግ መቆየቷን ጠቁመው÷ በተሟላ ሰላምና ደህንነት እየተካሄደ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
ከጸጥታ አንጻርም÷ የፌደራል ፖሊስ፣ ሪፐብሊካን ጋርድ፣ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ፖሊስን ያካተተው የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሀይል ዝጅቱን በተሟላ ሁኔታ አጠናቆ ወደስራ መግባቱን አረጋግጠዋል፡፡
የጸጥታ ሃይሎች በተናጠል እና በጋራ የሚሰሯቸው ሥራዎች መኖራቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡
ይህ ጉባኤ ባለፉት ወራት ሀገራችን ከነበረችበት ፈተናዎች አንፃር የብዙ ዓለም ሀገራትን እና መገናኛ ብዙሃን ዓይን ኢትዮጵያ ላይ እንዲያርፍ ያደርጋል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፡፡
እንግዶቻችን አዲስ አበባ እግራቸው ከረገጠበት ጊዜ አንስቶ ጉባኤውን አጠናቀው በሰላም ወደሀገራቸው እስከሚመለሱ ድረስ ሁሉም አካላት በቅንጅትና በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
ከጉባኤው ጋር በተገናኘ አሁንም የዓለም የጤና ስጋት ሆኖ የቀጠለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጉዳይ ትኩረት እንደተሰጠው በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
ከጉባኤው ተሳታፊዎች ጀምሮ ጉባኤውን ለመዘገብ የሚመጡ የሚዲያ ባለሙያዎች እንዲሁም እንግዶች በሚያርፉባቸው አገልግሎት መስጫ ተቋማትና በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች ህብረተሰቡ የኮቪድ ፕሮቶኮል ደንቦችን በማክበር እንደ ሃገር ቃል የተገባውን ስርጭቱን የመቆጣጠር ሃላፊነት ሊያግዝ ይገባል ብለዋል።
በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረግ ድጋፍን በተመለከተ በሶማሌ ክልል ድርቅ ባጋጠመባቸው ዘጠኝ ዞኖች 960 ሺህ ዜጎች ለድርቅ አደጋ ተጋላጭ በመሆናቸው ወደ ዕለት ደራሽ ዕርዳታ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ይህም በክልሉ ያለውን የእለት ደራሽ ድጋፍ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ3 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡
ከመስከረም እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ 558 ሺህ ኩንታል በላይ ምግብ ተልኮ ተሰራጭቷል፡፡ በዚህም ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ህዝብ በላይ ተጠቃሚ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በክልሉ ጉዳት ለደረሰባቸው 964 ሺህ አርብቶ አደሮች የተመጣጠነ ምግብ በማጓጓዝ ላይ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የዓለም ምግብ ኘሮግራም በበኩሉ 255 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍን በመለገስ በክልሉ ለሚገኙ 311 ሺህ ተጠቃሚዎች በጥሬ ገንዘብ መልክ ለማሰራጨት የቅድመ ዝግጅት ሥራ አጠናቋል ብለዋል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ባጋጠመ የድርቅ አደጋ ተጨማሪ ከ166 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ዕለት ደራሽ ዕርዳታ መርሃ ግብር እንዲካተቱ መደረጉን አብራርተዋል፡፡ ይህም አጠቃላይ የእለት ደራሽ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ዜጎች ቁጥር 426 ሺህ ያደርሰዋል ነው ያሉት፡፡
ባለፉት ወራት በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አማካኝነት 69 ሺህ ኩንታል ምግብ ተመድቦ በዞኑ ሲከፋፈል መቆየቱን ጠቁመው፥ በዚህም መሠረት ከተመደበው እርዳታ ከ41 ሺህ ኩንታል በላይ ምግብ ተሰራጭቷል ብለዋል፡፡
በተያያዘ በምስራቅ ባሌ በተመሳሳይ ባጋጠመ የድርቅ አደጋ ተጎዱ 251 ሺህ ወገኖች ለድርቅ ተጋላጭ መሆናቸው ተለይቶ 42 ሺህ ኩንታል የምግብ እርዳታ ተመድቦ በመጓጓዝ ላይ ነው ብለዋል፡፡
በደቡብ ክልል የደቡብ ኦሞ ዞን በተከሰተው ድርቅ 77 ሺህ ዜጎች ወደ ዕለት ደራሽ ዕርዳታ ማዕቀፍ እንዲገቡ ተደርጓል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ መንግስት በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች 11 ሺህ ኩንታል ምግብ መድቦ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የዞኑ ነዋሪዎች በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡
ወደ ትግራይ ክልል የሚላከው ሰብአዊ እርዳታ በተመለከተ ሰብአዊ እርዳታና መሰረታዊ ድጋፎችን ለማድረስ መንግስት ከአለም አቀፍ አጋር ተቋማት ጋር ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡
ወደ መቀሌ ከ41 በላይ የደርሶ መልስ በረራዎች በአለም የምግብ ፕሮግራም አማካኝነት መከናወናቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ አንስተዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!