የሀገር ውስጥ ዜና

የመንግስት የኤሌክትሮኒክ አገልግሎትን የመረጃ ደህንነት የሚያስጠብቅ ፖሊሲ እየተዘጋጀ ነው

By Meseret Awoke

February 01, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት የኤሌክትሮኒክ አገልግሎትን የመረጃ ደህንነት የሚያስጠብቅ “የኤሌክትሮኒክ መንግስት የኢንፎርሜሽን ደህንነት ፖሊሲ” እየተዘጋጀ ነው፡፡

ፖሊሲው የመንግስት አገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክ መንገድ ለዜጎች ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የመረጃ መረብ ደህንነትን ለማስጠበቅና በሁሉም ተቋማት ወጥነት ባለው መልኩ ለመተግበር የሚያስችል ነው፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለረቂቅ ፖሊሲው ተጨማሪ ግብዓቶችን ለመሰብሰብ ከፌደራል ተቋማት፣ ከክልልና ከግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ነው፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፥ የመረጃ መረብ ደህንነት ሥራ አመራር በአግባቡ ካልተመራ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውሶችን ስለሚያስከትል ፖሊሲው ይህንን ችግር ለመቅረፍና ወጥ የሆነ አሰራር ለመዘርጋት ያስችላል ብለዋል፡፡

በዓለማችን በተቋማት ላይ በሚፈጸም ጥቃት በደቂቃ 2 ነጥብ 9 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ይታጣል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ ፖሊሲው ኢትዮጵያ ለዚህ የሚመጥን ዝግጅት ለማድረግ እንደሚርዳት ተናግረዋል፡፡

ፖሊሲው በመንግስት መስሪያ ቤቶች በኩል ለዜጎች፣ ለሠራተኞች፣ ለንግድና ለሌሎች መንግስታዊ ተቋማት የሚተከሉ መሰረተ ልማቶችና የሚለሙ አገልግሎቶች በመረጃ መረብ ደህንነት ሥራ አመራር ደረጃ ወጥነት ባለው መልኩ ተግባራዊ እንደሚያስችል ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!