Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በፈረንሳይ የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በፈረንሳይ ሌቪን ትናንት ምሽት በተካሄደ የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል።

ኢትዮጵያውያኑ በ1 ሺህ 500 ሜትር በወንድ እና ሴት እንዲሁም በ3 ሺህ ሜትር ወንዶች በበላይነት ማጠናቀቅ ችለዋል።

በዚህ መሰረት በወንዶች 3 ሺህ ሜትር አትሌት ጌትነት ዋለ 7 ደቂቃ፣ ከ32 ሰከንድ፣ ከ80 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት አሸናፊ ሲሆን፥ አትሌት ሰለሞን ባረጋ 7 ደቂቃ፣ ከ33 ሰከንድ፣ ከ19 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት 2ኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።

ለባህሬን የሚወዳደረው ትውልደ ኢትዮጵያዊው አትሌት ብርሃኑ በለው 3ኛ ደረጃ ይዞ ውድድሩን ሲያጠናቅቅ፤ ኢትዮጵውያኑ አትሌት ለሜቻ ግርማ 4ኛ፣ በሪሁ አረጋዊ 5ኛ እንዲሁም ጥላሁን ሀይሌ 6ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች ደግሞ አትሌት ሳሙኤል ተፈራ 3 ደቂቃ፣ ከ35 ሰከንድ፣ ከ54 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ውድድሩን በአንደኝነት ማጠናቀቅ ችሏል።

በሴቶች በተካሄደው ውድድር ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ 4 ደቂቃ ከ60 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ውድድሩን በአንደኝነት ስታጠናቅቅ፤ አትሌት ለምለም ሀይሉ 4 ደቂቃ፣ ከ01 ሰከንድ፣ ከ57 ማይክሮ ሰከንድ 2ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

አትሌት አክሱማዊት አምባዬ ደግሞ 4 ደቂቃ፣ ከ03 ሰከንድ፣ ከ83 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት 3ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቃለች።

በ800 ሜትር በሴቶች በተካሄደ ውድድር ደግሞ አትሌት ሀብታም ዓለሙ 2 ደቂቃ፣ ከ03 ሰከንድ፣ ከ04 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ውድድሩን በሶስተኝነት ማጠናቀቋን የአፍሪካን አትሌቲክስ ዩናይትድ መረጃ ያመለክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

Exit mobile version