Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሀረሪ ከ780 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀረሪ ክልል ባለፉት 6 ወራት ከ780 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የክልሉ የኢንቨስትመንት፣ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ያህያ ገለጹ፡፡

 

በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያው 6 ወራት ለ41 ባሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት  ታቅዶ፥ ከ780 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 48 ባለሃብቶች ፈቃድ መሰጠቱን  ነው ኃላፊው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡

 

ባለሃብቶቹ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በሆቴል፣ በግብርናና በሌሎች ዘርፎች ለመሰማራት ባቀረቡት ፕሮፓዛል ፈቃዱ የተሰጣቸው  መሆኑን የገለጹት አቶ መሐመድ፥ በተለይም ከሌሎች ጊዜያት በተሻለ 11 ባለሃብቶች በማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃድ አግኝተዋ ብለዋል፡፡

 

ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከ136 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ  45 ባለሃብቶች ፈቃድ መሰጠቱን  ጠቁመው፥ ዘንድሮ ግን የተሻለ መሆኑንና ወደ ስራ ሲገቡም ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ ጠቁመዋል፡፡

 

ጽህፈት ቤቱ በክልሉ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችንና ምቹ ሁኔታዎችን በማስተዋወቅ ረገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ መሐመድ፥ በዚህም ክልሉ የቱሪስት መስህብና የንግድ ማዕከል እንደመሆኑ መጠን ባለሃብቶች በሆቴልና በንግድ ዘርፎች ቢሰማሩ ውጤታማ  ይሆናሉ ብለዋል፡፡

 

ከመሬት ጋር ተያይዞ ለኢንቨስትመንትና ለኢንቨስትመንት ነክ መሬት በጨረታና በምደባ በቅድሚያ የሚሰጥበት አሰራር እየተዘረጋ መሆኑንም  ተናግረዋል፡፡

 

በተሸመ ኃይሉ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version