አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 82ኛው የአገው ፈረሰኞች ማህበር የምስረታ በዓል በእንጅባራ ከተማ በዛሬው ዕለት ተከብሯል።
በዓሉ“ድልን በቻ ሳይሆን ጀግንነትንም እናወርሳለን!” በሚል መሪ ቃል ነው የተከበረው ፡፡
በበዓሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለን ጨምሮ የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የማህበሩ አለቃ ጥላዬ አየነው የአባቶቻችን ተግባርን በመድገም አሁንም ለህልውና ዘመቻው ፈረስ ሰግረን ባንዘምትም የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ወገንተኝነታችንን አሳይተናል ብለዋል።
“ፈረስ በአገው ምድር የተለየ ቦታ አለው፤ በሰላሙ ጊዜ ሰርግ ማድመቂያ፣ ታቦት ማጀቢያ፣ በለቅሶው አጽናኙ፣ የክብሩ መገለጫው ነው፥ ከሁሉ በላይ የአገው ገበሬ ሁለት ፈረስ ጠምዶ አራሽ ነው” ብለዋል።
የአገው ፈረሰኞች በዓልን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ ቅርሶች ለማስመዝገብ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው፥“ከአገው ህዝብ የምንማረው ብዙ ነገር አለ የመጀመሪያው ጽናት ነው፥ ለ82 አመታት ያለማቋረጥ የተደረገው ይህ በአል /ትርኢት/ ለአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ትምህርት ሰጪ ነው” ብለዋል።
ርእስ መስተዳድሩ አያይዘውም “አንድነታችንን አጠናክረን ለመሄድ የሚበግረን ነገር እንደሌለ ማሳያ የሆነ ህያው ትምህርት ቤታችን ነው” ብለዋል።
የአገው ፈረሰኞች ማኅበር የአገው አባቶች ከሌሎች አባት አርበኞች ጋር በመተባበር የጣልያንን ወራሪ ጦር ዓድዋ ላይ ድል መቀዳጀታቸውን ለመዘከር በየዓመቱ ጥር 23 በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚከበር በዓል ነው፡፡
ማኅበሩ በ1932 ዓ.ም ከ30 በማይበልጡ አባላት የተመሰረተ ሲሆን ÷ በአሁኑ ወቅት ከ59 ሺህ በላይ አባላትአሉት፡፡
በመዓዛ መላኩ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!