Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የጠ/ሚ ዐቢይ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ጉብኝት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ በሚጠናከርበት ጉዳዮች ላይ ለመምከር ያለመ ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ጉብኝት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ በሚጠናከርበት ጉዳዮች ላይና በቀጣይ በተለያዩ መስኮች የሁለቱ ሀገራት ዘላቂ ጥቅም በሚረጋገጥበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ያለመ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ልዑካን ቡድናቸው ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ አቡ ዳቢ ማቅናታቸው ይታወሳል፡፡

የልዑካን ቡድኑ ጋር ወደ ስፍራው የተጓዙት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ጉብኝት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በሚጠናከርበት ጉዳዮች ላይና በቀጣይ በተለያዩ መስኮች የሁለቱ ሀገራት ዘላቂ ጥቅም በሚረጋገጥበት ሁኔታ ላይ ለመወያየት እንዲሁም የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነትና ትብብር አሁን ካለበት ደረጃ ወደ ተሻለ ደረጃ በሚሸጋገርበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት የተባበሩት አረብ ኢምሬቶችና የኢትዮጵያ ግንኙነት እያደገ የመጣና ሁሉን አቀፍ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በነበረችበት ወቅት ችግሩን እንድታልፍ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ያደረገችው ድጋፍ ከፍተኛ ነበር ብለዋል፡፡

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአቡዳቢ ዘውዳዊ ልዑል እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መከላከያ ሰራዊት ምክትል ጠቅላይ አዛዥ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር በተወያዩበት ወቅት ምስጋና አቅርበዋል ነው ያሉት ዶ/ር ለገሰ ቱሉ፡፡

የአቡዳቢ ዘውዳዊ ልዑል መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ከችግሮቿ ወጥታ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለሷ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት እንዲሸጋገር ምኞታቸውን የገለጹት መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ለዚህም አበክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትም የበለጠ መጠናከር እንዳለበት በውይይቱ ማንሳታቸውን ዶክተር ለገሰ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመራው ልዑክ ዱባይ 2020 ዓለም አቀፍ ኤክስፖን የጎበኘ ሲሆን፥ ጉብኝቱ መሰል ኤክስፖ ሲዘጋጅ ምን ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባና ከሌሎች ለመማር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

በእስካሁኑም ቆይታ ከ500 ሺህ በላይ ሰዎች ኢትዮጵያ ይዛ የቀረበችውን ተመልክተዋል ፤ በእሱም ተደምመዋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ ፡፡

ኤክስፖው ኢትዮጵያ እራሷን ለዓለም ያሳየችበት መሆኑንም ነው ዶክተር ለገሰ ያመላከቱት፡፡

በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ በበኩላቸው ÷ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የቆየ መሆኑን ገልጸው፥ ነገር ግን ግንኙነቱ እየጠነከረ የመምጣው ባለፉት ጥቂት ዓመታት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ግንኙነቱም ዘርፈ ብዙ መሆኑን ያነሱት አምባሳደር ሱሌማን፥ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ የህዝብ ተጠቃሚነትን መፍጠር መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version