Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስና የትምህርት ተቋማትን ገንብቶ ለአገልግሎት ለማብቃት ከስምምነት ተደረሰ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሚኒስቴር ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮችና ከአስር ክልሎች ጋር በመሆን ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስና የወደሙ የትምህርት ተቋማቱትን ገንብቶ ለአገልግሎት ለማብቃት ከስምምነት ተደረሰ፡፡

በዚህም የትምህርት ሚኒስቴር ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮችና ከአስር ክልሎች የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታና ከትምህርትና ስልጠና ስራዎችን በሚመለከቱ ልዩ ልዩ አጀንዳዎች ዙሪያ ዛሬ ውይይት በማድረግ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡

በዚህም መሰረት፡-

1ኛ በወራሪው የህወሃት ቡድን የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮችና አስር የክልል ትምህርት ቢሮዎች ሚናን በተመለከተ ምንም እንኳን ቢሮዎቹ በክልላቸው በመደመር ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም በጦርነቱ ምክንያት በሁለቱ ክልሎች(በአፋርና በአማራ ክልሎች) እንደ ትምህርት ዘርፍ በጦርነቱ ክፉኛ የተጎዱ በመሆናቸው በክልሎቹ የሚገኙ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማስቻል በገንዘብ፣ በቁሳቁስ እንዲሁም በዓይነትና በማናቸውንም መንገዶች ድጋፍ ለማድረግ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡

እንዲሁም በተጎዱ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ይማሩ ለነበሩ የተፈናቀሉ ተማሪዎች ዙሪያ ከመማር ማስተማሩ ስራ ጋር በተገናኘ ሁሉም ክልሎች ድጋፍ ለማድረግ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

በመሆኑም ሌሎች ደረጃቸውን ያልጠበቁ ትምህርት ቤቶችን በአገራችን ውስጥ ባሉ ቁሳቁሶች፣ መልክዓ ምድርና የአየር ጸባይ ጋር በሚስማማ ሁኔታ በበጎ ፈቃደኘኝነት እያገለገሉ ባሉት የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር አማካኝነት በተዘጋጀው ደረጃውን የጠበቀው ዲዛይን መሰረት የሚሰራ እንደሚሆን ከስምምነት ተደርሷል፡፡

ስለሆነም ከዚህ በኋላ የሚገነቡ ትምህርት ቤቶች ደረጃ የጠበቀ እንዲሆን በውይይቱ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

2ኛ በጦርነቱ ምክንያት በአፋርና በአማራ ክልሎች ሙሉ በሙሉ ለወደሙት 1 ሺህ 93 ትምህርት ቤቶችና በከፊል የወደሙትና ጥገና የሚፈልጉ 3 ሺህ 220 ትምህርት ቤቶቸን ለመደገፍ ለሚቀጥሉት ጊዜያት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሚያደርጋቸው የሀብት ማሰባሰብ ስራዎች በሚገኙ የድጋፍ አቅሞቸ በሁለቱ ክልሎች ውስጥ ሙሉ በሙሉ የወደሙትን 1 ሺህ 93 ትምህርት ቤቶች የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊነት በመውሰድ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ሰርቶ የሚያስረክብ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

3ኛ. በአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም (GEQIP – E) በጀት ሃምሳ (50) ሞዴል ትምህርት ቤቶች በተቀመጠው መመዘኛ መሰረት በተመረጡ ክልሎች የሚገነቡ መሆናቸው ከክልል ትምህርት ቢሮ አመራሮቹ ጋር ስምምነት ተደርሷል፡፡

4ኛ በሁሉም ክልሎች በአጠቃላይ ሀምሳ(50 ) የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታን በተመለከተም ቀጣይ አገር መሪዎችን የምናፈራበት ፣ ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ተማሪዎችን የምናፈልቅበት ሁሉም ተማሪዎች በችሎታቸው ብቻ እየተመረጡ የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች ግንባታ በቶሎ ወደ ስራ እንዲገባ እንደሚደረግም በውይይቱ ተጠቅሷል፡፡

በእነዚህ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥም ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የ8ኛ ክፍል የትምህርት ውጤትን መሰረት ባደረገ መልኩ ትምህርት ቤቶቹ ተማሪዎችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ እንደሚሆን በውይይቱ ተጠቅሷል፡፡

ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግ የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴርና የየክልሎቹ የትምህርት ቢሮዎች ከወዲሁ በጋራ የሚሰሩ መሆኑ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ተደርጓል፡፡

በዘመን በየነ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version