Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአሸባሪው የህወሓት ወራሪ ቡድን ከወደሙ 87 ኢንዱስትሪዎች መካከል 27ቱ ሥራ መጀመራቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ጥር 19፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በአሸባሪው የህወሓት ወራሪ ቡድን ከወደሙ ኢንዱስትሪዎች መካከል 27ቱ ማምረት መጀመራቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገልጸዋል፡፡
ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች አሸባሪው የህወሓት ወራሪ ቡድን በደሴና ኮምቦልቻ በሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ላይ ያደረሰውን ጉዳት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በወቅቱ እንደተናገሩት ÷ ጉብኝቱ በዋናነት በሪፖርት የሚገለጹ መረጃዎችን በአካል በመመልከት መፍትሔ ለመስጠት ያለመ ነው፡፡
አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ኢንዱስትሪዎችን ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ወደ ሥራ ለመግባት የተዘጋጁ ድርጅቶችን ጭምር እንዳወደመ በጉብኝቱ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
ቡድኑ በኢንዱስትሪዎች ላይ ከፈጸመው ዝርፊያ ባሻገር ከፍተኛ ውድመት ማድረሱንም ገልጸዋል።
ይህም የኢንዱስትሪ ልማቱ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንዳይደግፍ ለማድረግ ሆነ ብሎ የፈጸመው ተግባር መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አሸባሪ ቡድኑ በአጠቃላይ 82 በማምረት ላይ የነበሩና 5 በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ላይ ውድመትና ዝርፊያ መፈጸሙን ገልጸው፣ ከእነዚህ መካከል 27ቱ ማምረት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ቢመለሱም የጥሬ ዕቃ፣ የመሥሪያ ካፒታል እና የመለዋወጫ ችግር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
ሥራ የጀመሩ ኢንዱስትሪዎች በመሉ አቅማቸው ወደ ምርት እንዲሸጋገሩና ሥራ ያልጀመሩት ደግሞ እንዲጀምሩ ሚኒስቴሩ ዝርዝር ጥናት አካሂዶ ለሚመለከታቸው አካላት ማስተላለፉንም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
Exit mobile version