Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶ ድጋፍ እያደረጉ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)  በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

በዞኑ 40 ሺህ ተፈናቃዮች አሸባሪው የህወሃት ቡድን በፈጠረው ጦርነት ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ቦታ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን  የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ እየሩስ መንግሥቱ ተናግረዋል።

በሁለት መንገድ ለተፈናቃዮች ድጋፍ እየተደረገ ነው ያሉት ሀላፊዋ፥ በዞኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አውስተው አሁን ላይ በወቅታዊ የፀጥታ ችግር ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረጉ ናቸው።

በዞኑ የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑ አለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ተፈናቃዮችን ምግብ ነክና ያልሆኑ ድጋፎችን በማቅረብ እየደገፉ ናቸው።

ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በዞኑ የተፈናቃይ ቦታ የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ መንግሥት ከሚያደርገው ድጋፍ ባለፈ ግብረሰናይ ድርጅቶችም የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ምክትል አስተዳዳሪዋ ገልፀዋል።

የዞኑ አስተዳደር ከተለያዩ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቀጣይ በሚሰሩ የመልሶ ማቋቋምና ሰብዓዊ ድጋፎች ዙሪያ ውይይት መደረጉ ተገልጿል።

መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በቀጣይ የተጠናከረ የሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ የማቋቋም ስራን እንደሚያከናውኑ ለዞኑ አስተዳደር በውይይቱ  ወቅት ገልፀዋል።

ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋምና ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት ከባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።

በምናለ አየነው

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

 

Exit mobile version