የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዕቅዱን ማሳካት ባለመቻሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይቅርታ ጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች የተቻላቸውን ጥረት ቢያደርጉም፤ ተይዞ የነበረውን እቅድ ማሳካት ባለመቻላቸው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ጠየቀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ በድን በካሜሮን አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ዋንጫ የነበረውን ተሳትፎ አስመልክቶ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና የፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን፥ በካሜሪኑ የአፍሪካ ዋንጫ ዋልያዊቹ ከምድብ የማለፍ እቅድ እንደነበር ጠቅሰው፥ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ይህን ማሳካት ባለመቻሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንጠይቃለን ብለዋል።
የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው፥ በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች “በውድድሩ ለማሸነፍ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል” ብለዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አክለውም፥ በውድድሩ ደርሶ ለመመለስ ሳይሆን ከምድቡ ለማለፍ እቅድ እንደነበራቸው መግለጻቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።
በውድድሩ የኢትዮጵያን ህዝብ እና ደጋፊዎችን የሚያስደት ውጤት ለማስመዘግብ የሚቻለውን ሁሉ ጥረት ማድረጋቸውን የገለጹት አሰልጣኙ፥ ሆኖም በዝግጅት ጊዜ ማነስ፣ በተጫዋቾች ቀይ ካርድ መውጣት እንዲሁም በቂ የወዳጅነት ጨዋታ ባለማድረጋችንና ሌሎች ተያየዥ ችግርች ምክንያት ያሰብነው አልተሳካም ብለዋል።
በትላልቅ ውድድሮች ላይ ተጨዋቾች ያላቸው ልምድ አናሳ መሆን ውጤቱ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩንም ጠቅሰዋል።
የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች የአካል ብቃት ችግርና የተገኙትን የግብ እድሎች አለመጠቀምም እንደ ችግር ተነስቷል።
በተለይ በአካል ብቃት በኩል ያለው ችግር በአጭር ጊዜ የሚፈታ ባለመሆኑ የረዥም ጊዜ ስራ ይጠይቃል ነው ያሉት አሰልጣኝ ውበቱ።
በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ከምድብ ጨዋታ የተሰናበተው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2 ጨዋታ ሲሸነፍ በአንድ ጨዋታ አቻ በመውጣት በ1 ነጥብ ነው ወደ አገሩ የተመለሰው።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!