Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሾሙ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 11 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሾሙ።

ሹመቱ ጨፌ ኦሮሚያ እያካሄደ ባለው መደበኛ ጉባኤ የጸደቀ ሲሆን፥ አቶ ሽመልስ አብዲሳም ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተሾሙት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሌሎች ሹመቶችን ለጨፌው እያቀረቡ ሲሆን፥ በዚህም ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አድርገው አቅርበዋል።

በጉባኤው የህዝቡ አንድነት እንዲጠናከርና የህብረተሰቡ ችግር እንዲቀረፍ እየተሰራ መሆኑ ተነስቷል።

አቶ ሽመልስ ባደረጉት ንግግርም ዜጎች ሀገር ወዳድ እንዲሆኑ የክልሉ መንግስትና በየደረጃው ያለው መዋቅር ይሰራል ብለዋል።

አያይዘውም በክልሉ የዜጎች መፈናቅል እንዳይኖር ሲሰሩ መቆየታቸውንም ጠቅሰዋል።

በኢኮኖሚው ረገድ ህግና ደንቦች አርሶ እና አርብቶ አደሩን መሰረት አድርገው ይወጣሉም ነው ያሉት አቶ ሽመልስ።

የህዝቦች መልካም ግንኙነት እንዲጠናከርና መቀራረብ እንዲኖር የሚሰራው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጨፌ ኦሮሚያ ሚያዚያ ወር 2011 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ እንደሾማቸው የሚታወስ ነው።

ጨፌው እያካሄደ ባለው ጉባኤ በዛሬው እለት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የረቂቅ ሕግ አዘገጃጀት ሥርዓትን ለመወሰን የወጣ አዋጅን ማጽደቁ ይታወሳል።

በአፈወርቅ አለሙ እና አዳነች አበበ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

Exit mobile version