Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጠ/ሚ ዐቢይ ከስልጤ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ከተወከሉ ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከስልጤ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ከተወከሉ ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ።

በውይይቱ ወቅት ተሳታፊዎች መንግሥት ከለውጡ ወዲህ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አድንቀዋል።

በተለይም በህዝቦች መካከል አንድነትን ለማጠናከር እና ሰላምን በሰላማዊ መንገድ ለማምጣት የሰራቸው ስራዎች ጠንካራ እንደነበሩ ገልጸዋል።

የዞኑ ህዝብ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የለውጥ ጎዳና ይደግፋል ያሉት ተሳታፊዎቹ፥ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን አንስተዋል።

በዚህም የመንገድ፣ የመብራት፣ የውሀ እና የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኔትወርክ ዝርጋታ እንዲሟላላቸው እና ኢስላማዊ የፋይናንስ ስርዓት እንዲመቻችም ጠይቀዋል።

ከዚህ ባለፈም የዞኑን በክልል የመደራጀት ጥያቄ እንዲሁም በዞኑ የኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲገነባም ጥያቄ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ማኒስትሩም ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፥ መንግስት የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በየአካባቢው በፍትሀዊ የሀብት ተደራሽነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የመብራት ሽፋን ዝቅተኛ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሀይል ማዳረስ በመንግሥት ብቻ ስለማይቻል የግሉ ባለሀብት በተናጠልም ሆነ በአጋርነት በዘርፉ እንዲሰማራም ጠይቀዋል።

ከመንገድ ጋር ተያይዞ ተደጋጋሚ ጥያቄ የተነሳበት የቆሼ ቢላሎ የአስፓልት መንገድ ግንባታ የኮንትራት ስምምነት ነገ ይፈረማልም ብለዋል።

መንግስት ለኢስላማዊ ባንክ አስቀድሞ ፈቃድ የሰጠ በመሆኑ የፋይናንስ ችግሮች ምላሽ ያገኛሉም ነው ያሉት በሰጡት ምላሽ።

ኢንዱስትሪ ፓርክ ከአዋጭነት አንጻር መንግስት አይገነባም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የግሉ ባለሀብት ሊሰማራበት እንደሚችል አውስተዋል።

በዚሁ መንገድ በዞኑ አንድ የቻይና የግል ኩባንያ ኢንዱስሪያል ፓርክ ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

በውይይቱ መጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡ በጅማ፣ በሀረርጌ፣ በሶማሌ ክልል እና በሌሎች አካባቢዎች ኅብረተሰቡ ለውጡን በመደገፍና የሀገራችንን ሰላም ማስቀጠልን የሚያሳስብ መልዕክት በማስተላለፉ አመስግነው መልዕክቱን ከልብ መቀበላቸውን ገልጸዋል።

የክልልነት ጥያቄዎችን በተመለከተ ቀደም ሲል ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰው፥ ጥያቄዎች በጥናት ላይ በተመሠረተ መንገድ እንደሚመለሱም አስረድተዋል።

በብሄር ብሔረሰቦች ቁጥር ክልል አይመሰረትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሕዝቡ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ እንደሚከበርለት አውስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ ማለዳ ላይ ነበር የዞኑ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ወራቤ የገቡት።

በወራቤ ስታዲየም ለተሰበሰቡ 60 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎችም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በአላዛር ታደለ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

Exit mobile version