አዲስ አበባ ጥር 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት 26 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 31 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 118 በመቶ ማሳካቱን ገለጸ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፥ የተበሰበው ገቢ ቀጥተኛ ከሆነ ታክስ 23 ነጥብ 73 ቢሊየን ብር፣ ቀጥተኛ ካልሆነው ታክስ 7 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር እና ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ 469 ሚሊየን ብር መሰብሰብ ተችሏል።
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከራሳቸው ይልቅ ሀገራቸውን በማስቀደም ግብራቸውን አሳውቀው በወቅቱ የከፈሉ ታማኝነታቸውና ሀገር ወዳድነታቸውን በተግባር ያሳዩ ከ95 በመቶ በላይ ታክስ ከፋዮችን በራሳቸውና በቢሮው ስም አመስግነዋል፡፡
የገቢ አፈጻጸሙ ሊሳካ የቻለው ከሚመለከታቸው አካላት በተለይ ከታክስ ከፋዩ ህብረተሰብ፣ ከቢሮው አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር መግባባት በመፍጠር ወደ ስራ በመገባቱ ነው ያሉት ኃላፊው፥ ከ420 ሺህ ታክስ ከፋዮች መካከል 296 ሺህ የደረጃ ‹‹ሐ›› ታክስ ከፋዮች አገልግሎትን ለማሳለጥ አዲስ ኢ-ታክስ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ በመደረጉ መሆኑን ነው ያስረዱት።
በቀጣይም የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ አፈጻጸምን ለማሳደግ፣ የስነ ምግባር ችግሮችን የመፍታት፣ የሐሰተኛ ደረሰኞች ቁጥጥር፣ ከንግድ ቢሮ ጋር በመተባበር ያለንግድ ፈቃድ የሚነግዱና ወደ ታክስ ስርዓቱ ያልገቡ ታክስ ከፋዮችን ስርዓት የማስያዝ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ችግሮች የመፍታትና ዘመናዊ የማድረግ እንዲሁም የቅንጅትና የግንዛቤ ስራዎች ይበልጥ የማጠናከር ስራዎች ትኩረት በመስጠት ይሰራል ማለታቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።