Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣የካቲት 10፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ እያካሄደች የሚገኘውን ለውጥ ለመደገፍ አሜሪካ ከፍተኛ ማዋዕለ ነዋይ እንደምታፈስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፔዮ አስታወቁ።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ጋር ተወያይተዋል።
 
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ውይይቱን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
 
በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ በማህበራዊ ፣ ፓለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እያካሄደች የሚገኘውን ማሻሻያ አሜሪካ እንደምትደግፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቀጣይም አሜሪካ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልፀዋል።
ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን አቶ ንጉሱ ተናግረዋል፡፡
 
ከዚህ ባለፈ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ እና ስለ ቀጣይ የትብብር አቅጣጫዎች መወያየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
 
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።
 
በእስካሁኑ ቆይታቸውም ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ተወያይተዋል።
 
በአላዛር ታደለ
Exit mobile version