Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአፍሪካ ሀገራት ምድር ጦር ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሀገራት ምድር ጦር ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ።

ለአራት ቀናት በሸራተን ሆቴል በሚካሄደው ጉባኤ ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ወታደራዊ አዛዦች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በጉባኤው ወታደራዊ አዛዦቹ በሀገራቱ መካከል ወታደራዊ ትብብርን በማጠናከር የአህጉሪቱን ደህንነት መጠበቅ ላይ ይወያያሉ።

ይህ ጉባኤ ሲካሄድ ስምንተኛው ሲሆን፥ የዘንድሮውን ጉባኤ ያዘጋጁት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት እና በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር በጋራ ነው።

የመጀመሪያው የአፍሪካ የምድር ጦር ኃይሎች ጉባዔ በአውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር 2010 በዋሽንግተን ዲሲ ነበር የተካሄደው።

ኡጋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ታንዛንያ፣ ማላዊ፣ ናይጄሪያ፣ ቦትስዋና በቅደም ተከተል ከሁለተኛ እስከ ሰባተኛ ጉባዔው የተካሄደባቸው ሀገራት ናቸው።

የዘንድሮው ጉባዔ “ለነገ ደህንነት ፍላጎት የዛሬ አመራር” በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

ከ40 በላይ የአፍሪካ አገራት ወታደራዊ አዛዦች የተሳተፉበት ጉባዔው የአፍሪካና የአሜሪካ የምድር ጦር ኃይሎች ወታደራዊ አዛዦች ሀሳብ የሚለዋወጡበት፣ የጋራ ችግሮቻቸውን በትብብር መፍታት የሚያስችል ግንኙነት የሚመሰርቱበት እንደሆነም ተገልጿል።

በጉባዔው መክፍቻ ላይ የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

አፍሪካ ከሽብር እንቅስቃሴ፣ ከባህር ላይ ውንብድና ጋር ተያይዞ የኃያላን አገራትን ትኩረት በመሳቧ በርካታ አገራት በአህጉሪቱ የጦር ሰፈር በመገንባት ላይ መሆናቸውን አውስተዋል።

በመሆኑም በአፍሪካ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የአፍሪካ የምድር ጦር ኃይሎች ጉባዔ አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ጄኔራሉ ተናግረዋል።

የአሜሪካ ጦር ተወካይ ጄኔራል ሚካኤል ጋሬትስ በበኩላቸው ፥የዛሬ መሪዎች ጠንክረው በመስራት ነገ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመመከት መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።

ወታደራዊ መሪዎች በሀገርና በቀጣና ደረጃ ሊኖራቸው የሚችለውን ሚና ጠንቅቀው ማወቅ እንዳለባቸው የጠቆሙት ጄኔራሉ ፥ለዚህም አስፈላጊውን የብቃት ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

የአሜሪካ ጦር ለአፍሪካ አቻው በስልጠና፣ በምክርና ተልዕኮዎችን በመደገፍ እያሳየ ያለውን አጋርነት ይበልጡኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

በተያያዘ ዜና በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለውን 8ኛውን የአፍሪካ ምድር ኃይል ጉባዔ በሚመለከት መግለጫ ተሰጥቷል።

በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር አዛዥ ሜጀር ጄነራል ሮጀር ክሉተር እንደገለጹት በአህጉሪቷ ለሚስተዋሉ ችግሮች ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባና ለዚህም አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ አንስተዋል።

የጉባዔው አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄነራል ጥላሁን አሸናፊም መድረኩ በአህጉሪቱ እያደገ የመጣውን ሽብርተኝነት ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን በጋራ መፍታት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ እንደሚመክር ገልጸዋል።

ተጨማሪ መረጃ ፦ ኢዜአ

Exit mobile version