ቴክ

በበዓላት ወቅት ሊወሰዱ የሚገቡ የሳይበር ደህንነት ጥንቃቄዎች

By Meseret Awoke

January 05, 2022

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የበዓላት ወቅቶች ከሌሎች ጊዜያት በተለየ መልኩ የሳይበር ወንጀለኞች በቀላሉ የመረጃ ጥቃቶችን ለማድረስ የተመቹ ወቅቶች ናቸዉ፡፡

በዓልን ጠብቀዉ በሚፈጸሙ ሳይበር ጥቃቶች ሳቢያም የገንዘብ ስርቆት፣ የማንነት ስርቆት እና የማጭበርበር ተግባራት በስፋት እንደሚስተዋሉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ገልጿል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ ብዙዎች የኦንላይን ግብይቶችን በቴሌግራም፣ በፌስቡክ፣ በዋትስአፕ፣ ኢንስታግራም እና በመሳሰሉት ማህበራዊ የትስስር ገጾች በስፋት እየተዋወቁ እና ግብይቶች እየፈጸሙ ያሉበት ወቅት ነዉ፡፡

ይህ ሁኔታም በበዓል ወቅት ሸማቾች በመረጃ መንታፊዎች እና አጭበርባሪዎች እጅ ላይ ሊወድቁ ስለሚችሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በበዓላት ወቅት በመረጃ መንታፊዎች እና አጭበርባሪዎች እጅ ላይ እንዳይወድቁ ሊያደርጓቸዉ የሚገቡ የጥንቃቄ እርምጃዎች ዉስጥ የሚከተሉት ቀርበዋል፡፡

ወደ መልዕክት መቀበያ ሳጥኖዎት የሚላክሎትን አጠራጣሪ አገናኞች ፣ አባሪዎች እና ሌሎች መልእክቶችን ከመክፈትዎ በፊት በጥንቃቄ ያጢኑ፡፡

በበዓላት ወቅት የመረጃ ጠላፊዎች ኣጥፊ ተልእኮ ያላቸዉ ሰነዶችን፣ ደረሰኝ፣ ስጦታ፣ ዝመና ወይም የትዕዛዝ መረጋገጫ በማስመሰል ሊልክልዎት ይችላሉ፡፡

በኢ-ሜይል ለሚላክልዎት ቅጽ ወይም አገናኝ የይለፍ-ቃልዎን ወይም የፋይናንስ መረጃዎን አያስገቡ፡፡

ስጦታ ሲቀበሉም ሆነ ሲሰጡ ጥንቃቄ ያድርጉ ፤ በዚህ በዓል ቴክኖሎጂ ነክ ስጦታ እየተቀበሉ ወይም እየሰጡ ከሆነ የሚጠቀሙበት ቁስ የዘመነና የቅርብ ጊዜ ሶፍትዌር ያለው መሆኑን ያረጋግጡ፡፡

ጊዜያቸው ያለፈባቸው ሶፍትዌሮች ተጋላጭነቶችን የያዙ ሊሆኑ ይችላሉ ፤ ያዘምኑ።

ያገለገለ ቁስ እየተቀበሉ ወይም እየሰጡ ከሆነ ከመስጠትዎ ወይም መጠቀም ከመጀመርዎ በፊት መሳሪያውን ወደ መጀመሪያ የፋብሪካ ምርት ሥርዓት መመለስዎን ያረጋግጡ፡፡

የበይነ መረብ ጋር የተቆራኙ ቁሶችን ደህንነት ለመጠበቅ የሳይበር ደህንነት ማስጠበቂያ እርምጃዎችን ይውሰዱ፡፡

ከበይነ-መረብ ጋር የተቆራኙ ቁሶች ደካማ የሚባል የደህንነት ጥበቃ ሪከርድ ያላቸው በመሆኑ የቁሶችን ደህንነት በአግባቡ አለማስጠበቅ ለአጥፊዎች ይበልጥ ሥራቸውን ቀላል እያደረጉላቸው መሆኑን አይዘንጉ፡፡

በመሆኑም በቁሶቹ ላይ ከሚገኙ የደህንነት ሥርዓቶች በባለብዙ ደረጃ የማንነት ማረጋገጫ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ፤ በቁሶቹ ላይ የነበረውን ነባሪ የይለፍ-ቃል ይቀይሩ ፤ የዘመነ ሶፍትዌር ይጠቀሙ ሲልም ኤጀንሲው አስገንዝቧል፡፡