ቢዝነስ

ለገና በዓል ጤንነቱና ጥራቱ የጠበቀ የእርድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል

By Mekoya Hailemariam

January 05, 2022

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለመጪው የገና በዓል ጤንነቱና ጥራቱን የተጠበቀ የእርድ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ መዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ገለጸ።

የድርጅቱ የኮሙኒኬሽን ባለሞያ ወይዘሪት ርብቃ ማስረሻ በሰጡት መግለጫ፥ ለበዓሉ ከአምስት ሺህ በላይ የበግ፣ የፍየልና የቀንድ ከብቶች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

ጎን ለጎንም ጤንነቱንና ጥራቱ የተጠበቀ ሥጋን ለኅብረተሰቡን ተደራሽ ለማድረግ በቂ ዝግጅት የተደረገባቸው የእርድ ማዕከላት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ማዕከላቱ በኬሚካል መጽዳታቸውን ጠቁመው ከኮሮና ቫይረስና ከሌሎች በሽታዎች ለመከላከል የእርድ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሞያዎች የጤና ምርመራ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በዓሉን ተከትሎ የሚከሰት የዋጋ ንረትን ለመቀነስ አራት ሉካንዳ ቤቶች በድርጅቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

“ለገና በዓልና ከውጭ የሚገቡ ዳያስፖራ ወገኖች” ባህላዊ ሥርዓቱን የተከተለ ጤንነቱ የተረጋገጠ ሥጋ እንደሚያቀርቡ የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ሉካንዳ ነጋዴዎች ሰብሳቢ አቶ አየለ ሳህሌ ናቸው።

በተለይም ዳያስፖራው ለረጅም ዓመት የሚናፍቀውን ጥሬ ሥጋ የመመገብ ባህል ያለ ምንም ሥጋት የሚመገብበትን አገልግሎት ለማቅረብ ከሉካንዳ ቤቶች ጋር ሥምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

ማንኛውም ነጋዴ ለኅብረተሰቡ የሚያቀርበው ሥጋ ምንም አይነት የዋጋ ማሻሻያ እንደማያደርግና የአቅርቦት እጥረት እንደማይኖር አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ኅብረተሱቡ በሕገ-ወጥ እርድ የሚቀርቡ ሥጋዎችን ባለመመገብ ጤናውን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

በመዲናዋ የሚከሰቱ ሕገ-ወጥ እርድ ለመከላከል ከደንብ ማስከበርና ከፖሊስ ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ጠቅሰው ኅብረተሰቡም ጥቆማ በማድረግ እንዲተባበር ድርጅቱ ጥሪ አቅርቧል።

በአዲስ አበባ ሕገ-ወጥ እርድ ከሚያስከትለው የጤና ችግር ባለፈ መንግሥት በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ እንደሚያጣ ድርጅቱን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

 

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!