አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 13ኛው የኢትዮጵያ የከተሞች የመጠጥ ውኃና ሳኒቴሸን ፎረም በወላይታ ሶዶ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
የመጠጥ ውኃና ሳኒቴሸን ፎረሙ “የራስን አቅም በማጠናከር በኢትዮጵያ ወስጥ በሚገኙ ከተሞች የውኃ እና ሳኒቴሸን አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ ያለው።
በፎረሙ ማስጀመሪያ ላይ 50 ሚሊየን ብር የፈጀው የሶዶ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውኃና ሳኒቴሸን የማስፋፊያ ፕሮጀክት የተመረቀ ሲሆን፥ የሰው ሰራሽ ኃይቅና የውኃ ማሸጊያ ፋብሪካ የመሰረት ድንጋይ በውኃ መስኖና ኢኒርጂ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ ተቀምጧል።
የሰው ሰራሽ ሀይቁ 120 ሄክታር መሬት የሚሽፍን ሲሆን፥ ከ80 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ይደረግበታል ተብሎም ይጠበቃል።
ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ለ3 ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥርም ተጠቁሟል።
በፎረሙ ላይ የተገኙት የውኃ መስኖና ኢኒርጂ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ፥ የወላይታ ሶዶ ከተማ ባለፈው ዓመት ለደንበኞቹ ንፁህ ውኃን በማቅረብ ከደሴ ቀጥሎ ሁለተኛ መሆኗን በማስታወስ፥ በሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ልምድ በመለዋወጥ በውኃና ሳኒቴሸን ዘርፍ ለነዋሪዎቻቸው የላቀ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።
የደቡብ ክልል ውኃና መስኖ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በበኩላቸው፥ እንዲህ ዓይነቱ መድረክ የውኃ አገልግሎቶች እርስ በእርስ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉና በጎ ተሞክሮዎችን በመቀመር ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲያቀርቡ የሚረዳ ነው ብለዋል።
ከፍተኛ የሆነ የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር የሚታይባቸውን ከተሞች በመለየት ተጠቃሚ ለማድረግ በተያዘው ዕቅድ መሠረት የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ችግር ከሚታይባቸው ከተሞች መካከል የወላይታ ሶዶ ከተማ አንዷ በመሆኗ መንግሥት ዘላቂ የንጹህ መጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ተጠቃሚ አድርጓታልም ነው ያሉት።
በዚህም በነዋሪዎች ዘንድ ትልቅ ቅሬታ ሲያስነሳ የነበረው የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር መቀረፉ ከከተማው ነዋሪ ባሻገር በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች መሠማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ትልቅ እፎይታ መስጠቱን ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ የከተማዋ የንፁህ መጠጥ ውኃ ሽፋን 95 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።
ፎረሙ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ ንፁህ የመጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን አገልግሎቶችን ለማዘመን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር በማድረግ ቀጣይ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በጥላሁን ሁሴን
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision