የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌደሬሽን 21ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አከናወነ
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 21፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌደሬሽን ዛሬ ባከናወነው 21ኛ ጠቅላላ ጉባኤ የተለያዩ አጀንዳዎች ቀርበው ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ጉባዔውን የመሩት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ፍትህ ወልደ ሰንበት (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የዞን አምስት እጅ ኳስ ሻምፒዮና እንድታዘጋጅ ብትመረጥም ሀገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ውድድር ለማከናወን አመቺ አይደለም በሚል አዘጋጅነቷን እንደተነጠቀች ተናግረዋል።
ነገር ግን ሀገሪቱ ሰላም እንደሆነች በማስረዳት ውሳኔያቸውን እንዲቀለብሱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌደሬሽን ስፖርቱ በሁሉም ክልሎች እና ከተማ መስተዳደሮች እንዲስፋፋ እንዲሁም ተሳታፊ ክለቦች እንዲበራከቱ እየሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል።
በተያያዘም ስድስተኛ ዓመቱን የያዘው የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ነገ በአዲስ አበባ በትንሿ ስታዲየም እንደሚጀመር ተገልጿል።
በውድድሩ 10 ክለቦች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ከፌዴሬሽኑ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።