የሀገር ውስጥ ዜና

ከባለሃብቶችና በጎ ፈቃደኞች የተሰበሰበው የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ለሴት ተማሪዎች እየተሰጠ ነው

By Tibebu Kebede

February 17, 2020

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከባለሃብቶች እና ከበጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች የተሰበሰበው የሴቶች ሞዴስ እና ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች በመንግስት ትምህርት ቤት ለሚማሩ ሴት ተማሪዎች እየተሰጠ መሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

በአስተባባሪ ቢሮዎች አማካኝነት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በለቡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚማሩ ሴት ተማሪዎች የሴቶች ሞዴስ እና ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶቹን ማስረከቡን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ሓላፊ እና የአስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ አብርሃ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት፥ በሀገራችን 70 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ የመግዛት አቅም የላቸውም።

በተጨማሪም 50 በመቶ ሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ ባለማግኘታቸው ብቻ ከትምህርታቸው እንደሚስተጓጎሉ ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የተማሪዎችን በተለይ የሴት ተማሪዎችን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ የትምህርት ቤት ምገባ፣ የደንብ ልብስ ፣ የትምህርት ቁሳቁስ እና የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየሰራ መሆኑን መግለፃቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የሞዴስ እና ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው ሴት ተማሪዎችም በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ የሴት ተማሪዎችን ችግር በአግባቡ ተገንዝቦ ባደረገው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸው በትምህርታቸው ጠንክረው እንደሚማሩ ተናግረዋል።