አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አልጋ ወራሽ ሼክ መሀመድ ቢን አል ነኸን ጋር ተወያዩ።
በዚህም ወቅት ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ በሚያደርጉ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
የሀገራቱ ግነኙነት አሁን የደረሰበትን ደረጃ በማድነቅም በቀጣይ የበለጠ እንዲጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው ነው ያመለከቱት።
ከሁለትዮሸ ጉዳዮች በተጨማሪም አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችንም አንስተው ሀሳብ ተለዋውጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጉብኝታቸውንም አጠናቀዋል።
በዚህ ጉብኝታቸውም በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በህገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውንን ህጋዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በሀገሪቱ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያ ያሉባቸው ችግሮች እንዲፈቱ ከስምምነት ተደርሷል።
ከዚህ ባለፈም በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ልጆች የሚማሩበት ትምህርት ቤት ለመክፈት ከስምምነት ተደርሷል።
በጉዞው በተደረገ የዲፕሎማሲ ስራም በአቡዳቢ ለኢትጵዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ህንጻ ማሰሪያ ቦታም ተፈቅዷል።
በዱባይ እና ሻርጃ ግዛቶች አማካይ ስፍራ ለፕሮቴስታንት አማኞችም የጸሎት ቦታ በኤክስፖ 2020 ከሚሰራ ህንፃ እንዲሰጥ መወሰኑን በሀገሪቱ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ተናግረዋል።
በአልአዛር ታደለ