አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ከለቡ ጀሞ የተሰራውን የሞተር አልባ ትራንፖርት አገልግሎት መስጫ መንገድ ስራ መጀመሩን የከተማዋ የትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት የጀመረው ነዋሪው ብስክሌትን እንደ አንድ የትራንስፖርት አማራጭ እንዲጠቀም ታስቦ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ስጦታው አካለ ተናግረዋል።
ለከተማዋ የሚመጥን የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን በዓይነትና በብዛት ተደራሽ ማድረግም አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም በቅርቡ ከቃሊቲ- ቱሉ ዲምቱ 11 ኪሎ ሜትር መንገድ እና ከሃይሌ ጋርመንት- ጀሞ 4 ኪሎ ሜትር መንገድ ተመሳሳይ የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት ይጀመራል ብለዋል።
በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቃው ከለቡ-ጀሞ የተሰራው የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ መንገድ የ2 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ እንዳለው ነው የተነገረው።
ከዚህ ጎን ለጎን በከተማዋ “አብነት” እና “ስታዲየም” አካባቢዎች የብስክሌት መለማመጃ ቦታዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በመጪዎቹ 10 ዓመታት የ100 ኪሎ ሜትር የብስክሌት ትራንስፖርት መስመር ለመዘርጋት መታቀዱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት በሰዎች የአካል እንቅስቃሴ ማነስ ምክንያት ለሚመጣ የጤና ችግር፣ ወጪ ለመቀነስና የአየር ብክለትን ለመከላከል ጉልህ ፋይዳ አለው።
መንገዱ ለብስክሌት ተጠቃሚዎች ተደራሽ መደረጉ ለጤናማ እንቅስቃሴ፣ የመንገድ መዘጋጋትን ለመቀነስ፣ ለመዝናናት፣ የድምጽና የአየር ብክለትን ለመቀነስ ትልቅ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።
ምንጭ፡- ኢዜአ