Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሱዳን ገዳሪፍ ግዛት እና ጎንደር ከተማ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰራ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በሱዳን ገዳሪፍ ግዛት እና ጎንደር ከተማ መካከል ያለውን የንግድ፣ባህል እና ፖለቲካ ግንኙት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰራ ተገለጸ።

በገዳሪፍ ዋና አስተዳዳሪ ሜጀር ጀኔራል ነስረዲን አብዲ የተመራ ልዑክ በትናንትናው ዕለት ጎንደር ከተማ መግባቱ ይታወቃል።

የልዑካን ቡድኑ በዛሬው ዕለት ከጎንደር ከተማ አመራሮች ጋር በሱዳን የገዳሪፍ ግዛትና በጎንደር ከተማ መካከል ያለውን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ተወያይቷል፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ማስተዋል ስዩም፥የኢትዮጵያና ሱዳን ህዝቦች ለረጅም ዓመታት በአንድነት፣በወንድማማችነት እና በመተሳሰብ የኖሩ መሆናቸውን አውስተዋል።

በሀገራቱ መካከል ያለውን ማህበራዊ ፣ፖለቲከዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።

በገዳሪፍ ግዛት እና በጎንደር ከተማ መካከል የሚፈጠረው የባህልና የንግድ ግንኙነትም ለጎንደርና ለገዳሪፍ ግዛት ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።

ግንኙነቱን ለማሳደግም የገዳሪፍ ግዛት ነጋዴዎች የሚሳተፉበት የንግድ ባዛር በጎንደር ከተማ የሚዘጋጅ መሆኑን ምክትል ከንቲባው ጠቁመዋል።

የጎንደር ከተማ ልዑካን ቡድኑም ወደ ግዛቷ በማቅናት የተለያዩ ተሞክሮዎችን እንደሚቀስም መናገራቸውን ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የገዳሪፍ ግዛት ዋና አስተዳዳሪ ሜጀር ጀኔራል ነስረዲን አብዱል ከሪም በበኩላቸው፥በሱዳንና ኢትዮጵያ መተማ የሚባል የቦታ ስያሜ መኖሩን በመጥቀስ ይህም ሁለቱ ሀገራት ተመሳሳይ ባህል ያላቸው መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ሀገሬ ውስጥ ያለሁ ያህል ይሰማኛል ያሉት አስተዳዳሪው፥የልዑካን ቡደኑ ጉብኝት በገዳራፍ ግዛትና በአማራ ክልል መካካል ያለውን ግንኙት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ልኡካኑ በገዳራፍ ግዛት እና በአማራ ክልል መካከል ያለውን የሰላም፣ልማትና ፖለቲካ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ በቅንጅ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

Exit mobile version