ስፓርት

ማንቼስተር ሲቲ ከአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ለሁለት አመት ታገደ

By Tibebu Kebede

February 15, 2020

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የእንግሊዙ እግር ኳስ ክለብ ማንቼስተር ሲቲ ለቀጣዮቹ ሁለት አመታት በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ እንዳይሳተፍ ታገደ።

ክለቡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበርን የገንዘብ አስተዳደር (የፋይናንሺያል ፌር ፕሌይን) አላከበረም በሚል ነው እገዳው የተጣለበት።

እገዳውን ተከትሎም ክለቡ በቀጣዮቹ ሁለት አመታት በትልቁ የክለቦች ውድድር አይሳተፍ፤ ይህም ክለቡን እስከ 170 ሚሊየን ፓውንድ ያሳጣዋል ተብሏል።

የአሁኑ እገዳ ከፈረንጆቹ 2012 እስከ 2016 ክለቡ ከስፖንሰር ሺፕ ገቢ አገኘሁት በሚል ለእግር ኳስ ማህበሩ ያቀረበው የገንዘብ መጠን የተሳሳተና የተጋነነ መሆኑን ተከትሎ የተጣለ መሆኑም ተገልጿል።

ከዚህ ባለፈም የክለቦችን የገንዘብ አስተዳደር የሚቆጣጠረው የማህበሩ አካል ለሚያደርገው ማጣራት ተባባሪ ባለመሆኑ እገዳው ተጥሎበታልም ነው የተባለው።

ክለቡ ከውድድር ከመታገዱ ባሻገር 25 ሚሊየን ፓውንድ የገንዘብ ቅጣትም ተጥሎበታል።

የእንግሊዙ ክለብ በውሳኔው ቅሬታውን የገለጸ ሲሆን፥ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ግልግል ፍርድ ቤት እወስደዋለሁ ብሏል።

ምንጭ፡-ደይሊ ሜይል

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision