Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአንዳንድ ምእራባውያን ሀገራት “የዘር ማጥፋት” ፖለቲካ ሴራ ሲፈተሽ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዬል ማክሚላን ማዕከል “በሰሜን ኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር ምላሽ መስጠት” በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት አዘጋጅቶ ነበር፡፡

በውይይቱም ሴናተሮችን፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ዳይሬክተሮች እና ፕሮፌሰሮች ተጋባዥ እንደነበሩ ተገልጿል፡፡

ጥላሁን እምሩ ፥ በውይይት መድረኩ ሴናተር ክሪስ ኩንስ፣ የዴላዌር እና የዬል የህግ ትምህርት ቤት ምሩቃን ተወካይ፣ የሰሜን ካሮላይና ሪፐብሊካን ሴናተር ቶም ቲሊስ እንዲሁም የዬል የዘር ማጥፋት ጥናቶች ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ዴቪድ ሳይመን ተገኝተው በጉዳዩ ላይ ንግግር ማድረጋቸውን ጽፏል፡፡

የዬል ማክሚላን ማዕከል ያዘጋጀውን ውይይት በኢትዮጵያ ጥላቻ የሰከረችው ኒማ ኤልባጊር ማስተናበሯንም ጥላሁን እምሩ አመላክቷል፡፡

ኒማ ኤልባጊር፥ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በወረራቸው የአማራና የአፋር ክልሎች የፈጸማቸውን በጭካኔ የተሞሉ ጭፍጨፋዎች፣ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እና ዝርፊያዎች እያየች እንዳላየ እና ምንም እንዳልተፈጠረ ስታልፍ የነበረች እና በትግራይ ክልል ተፈጸመ በተባለው ጉዳይ ላይ በርካታ የሃሰት ዘገባዎችን ሥትሰራ የቆየች ጋዜጠኛ መሆኗ ይታወሳል፡፡

ጋዜጠኛዋ ከኢትዮጵያ መንግስት የተላለፈውን የአንድ ወገን የተኩስ አቁም እና የሠላም ጥሪ በቀለኛው የህወሓት አሸባሪ ቡድን እንደቀለበሰውና አፋርንና አማራን በመውረር ለዓለም ግልጽ የሆነ ወንጀል እንደፈጸመ እንኳ አልዘገበችም፡፡ ይህም በጋዜጠኝነት ሥነ ምግባሯ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ሆኖ አልፏል፡፡

በሌላ በኩል ጋዜጠኛዋ ሱዳናዊት እንደመሆኗ እና በሱዳንና በኢትጵያን አዋሳኝ ድንበር ላይ ውዝግብ እንደመነሳቱ ብሎም ሱዳንና ግብጽ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ላይ ከኢትጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ እንደመግባታቸው መጠን፣ ከጋዜጠኛዋ ባህሪ ጋር ተደምሮ አሸባሪው የህወሓት ቡድን የፈጸማቸውን በደሎች ገለልተኛ ሆና ትዘግባለች ተብሎም እንደማይጠበቅ ነው የተገለጸው፡፡

ከእውነታው በተቃረነ መልኩ ይህን መድረክ ያስተናበረችው የሲ ኤን ኤኗ ኒማ ኤልባጊር ፣ ስለ ኢትዮጵያ የጻፈቻቸው የተለያዩ ሥራዎች የመረጃ ውስንነቶች እና ከባድ ክፍተቶች የነበሩባቸው እንደሆኑ መረጃዎች እያመላከቱ ዬል ያዘጋጀውን መድረክ እንድትመራ መመረጧ አግራሞት ያጭራል ነው ያለው – ጸሃፊው፡፡

ጋዜጠኛዋ፥ የኢትዮጵያ መንግሥትና የአማራ ልዩ ኃይሎች የትግራይ ተወላጆችን እየጨፈጨፉ አስከሬናቸውን በተከዜ ወንዝ ጥለዋል በማለት ሁኔታውን በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ወቅት በካጄራ ወንዝ ከተጣሉት የቱትሲ አስከሬኖች ጋር ለማመሳሰል እና የሰዎችን አመለካከት ለመቀየር እንደሰራችም ጥላሁን እምሩ በጽሁፉ አንስቷል፡፡

በወቅቱም የጭፍጨፋውን ክስ ለማጣራት ወደ ቦታው ያቀናው የሲኤን ኤን ወንጀል መርማሪ ደግሞ የጥርስ ሐኪም መሆኑ ግርምት ፈጥሮ እንደነበርም ጸሃፊው አስታውሷል፡፡

የዬል ማክሚላን ማዕከል ፥ በኢትጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያጠኑትን እና ጥልቅ እውቀት ያላቸውን የዊልፍሪድ ላውሪየር ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር እና የባልሲሊ ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አን ፊትዝ ጀራልድን በውይይት መድረኩ እንዲሰታፉ ያቀረበውን ግብዣ መሰረዙ ጥያቄ አስነስቷል ብሏል ጸሃፊው፡፡

የዬል ማክሚላን ማዕከል ÷ ይህን ያደረገው ኒማ ያዘጋጀችውን ውሸትና ዕቅድ ፕሮፌሰሯ የሚያቀርቡት ማስረጃ ውድቅ ስለሚያደርገው አቅጣጫ ያስቀይርብኛል ብሎ መሆኑን መገንዘብም አይከብድም ሲልም ጥላሁን አመክንዮውን ያጠናክራል፡፡

ጸሃፊው፥ በመድረኩ ኢትዮጵያውያን በሥጋት እየኖሩ ነው የሚሉ ሃሳቦችና ሴናተሮች በኢትጵያ ላይ ያላቸውን ፖለቲካዊ ፍላጎት ለመጫን የሚሄዱበትን ርቀት፣ ተንኮል እና ሴራ እንዲሁም የውጪ መገናኛ ብዙኃኑ ውሸት በማቀነባበር የዓለሙን ማኅበረሰብ አመለካከት ለመቀየር የሚሠራው ሥራ በውይይት መድረኩ አዘጋጅ ፕሮፌሰር ዴቪድ ሳይመን፣ በሴናተር ክሪስ ኩንስ እና በመገናኛ ብዙኃኑ ሲኤንኤን ተንጸባርቋል ነው ያለው፡፡

የፓነል ውይይቱ በዬል ማክሚላን ማዕከል አዘጋጅነት፣ በኒማ ሃሳብ እና በሲኤን ኤን የተቃኘ እና አበረታች የመፍትሄ ሃሳብ ከተጋባዦች ያልተገኘበት ሆኖም አልፏል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version