አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሱዳን በፈረንጆቹ 2000 በአሜሪካ መርከብ ላይ በደረሰው ፍንዳታ ተጎጂ ለሆኑ 17 ቤተሰቦች ካሳ ለመክፈል ተስማማች።
በወቅቱ ዩ ኤስ ኤስ ኮል በተባለችው መርከብ ላይ አልቃይዳ በየመን ወደብ በፈጸመው ጥቃት 17 የአሜሪካ ባህር ሃይል አባላት መሞታቸው ይታወሳል።
አሜሪካም ጥቃት ፈጻሚዎቹ ሁለቱ አጥፍቶ ጠፊዎች በሱዳን የሰለጠኑ ናቸው በሚል ለጥቃቱ ካርቱምን ተጠያቂ አድርጋት ነበር።
ሱዳን በበኩሏ ከጥቃቱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላት በመግለጽ ስታስተባብል ቆይታለች።
ከረጅም አመታት በኋላም አዲሱ የካርቱም መንግስት ካሳ ለመክፈል ተስማምቷል።
አሁን ላይ ሱዳን ለሟች ቤተሰቦች ካሳ ለመክፈል ከመስማማቷ ባለፈ ግን ምን ያክል ገንዘብ እንደምትከፍል የታወቀ ነገር የለም።
ሬውተርስ ለመረጃው ቅርብ ካላቸው ምንጮች አገኘሁት ያለው መረጃ ደግሞ ሱዳን እስከ 30 ሚሊየን ዶላር ካሳ ለመክፈል መስማማቷን ያመላክታል።
አሜሪካ ሱዳንን ሽብርተኝነት ትደግፋለች በሚል በጥቁር መዝገብ ውስጥ እንዳሰፈረቻት ይታወቃል።
የአሁኑ እርምጃም አሜሪካ በሱዳን ላይ የያዘችውን አቋም እንድታለዝብ ያደርጋታል ተብሎ ታምኖበታል።
ምንጭ፡-ቢቢሲ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision