አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህግ የበላይነትን ማስከበር ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ እንዳይደለ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገለፀ።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ በሀገሪቱ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተወሰዱ እና ሊወሰዱ ስላሉ እርምጃዎች መግለጫ አውጥቷል።
ለሀገሪቱ ደህንነትና ለህዝቡ ህልውና ሲባል ከዚህ በኋላ ማናቸውንም በወንጀል ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ አካላትን እንደማይታገስ ጽኑ አቋም ተይዟል ብሏል።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
ከኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተሰጠ መግለጫ
የህግ የበላይነትን ማስከበር ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የፍትህ ስርዓቱን የማጠናከርና የህግ የበላይነትን የማክበርና የማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ ለማስቀጠል ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ይታወሳል፡፡ በተለይም መንግስት የሕግና የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻልና በዘርፉ አሳታፊነትን ለማጎለበት በሰጠው ትኩረት መሠረት ከመንግስት መዋቅር ውጭ ከፍተኛ ልምድና ብቃት ያላቸውን የሕግ ባለሙያዎች ያካተተ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ በማቋቋም የሰብዓዊና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ሊያሰፉ የሚችሉ ህጎች ላይ ማሻሻያ አድርጓል።
አንዳንዶቹ ከ20 ዓመት በላይ ለማሻሻል ተብሎ ከፍተኛ የሀብት ብክነት ሲፈፀምባቸው የነበረው በአማካሪ ጉባኤ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲሻሻል የተደረጉት ተጠቃሽ ናቸው።
የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትና ህዝባችን በፍትሕ ሥርዓቱ ያለውን አመኔታ ለማሻሻል በተወሰደው የማሻሻያ እርምጃ ለህዝባችን ተስፋን ያሰነቁ ተግባራት ተፈፅመዋል።
በሌላ በኩል የህግ ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ ጋር በተያያዘ በከባድ ሰብአዊ መብት ጥሰት፣ በጅምላ ጭፍጨፋ እና ከባድ የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የዚህ ድርጊት ተሳታፊ የሆኑ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይ ተደርጓል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተበራከቱ የመጡ የወንጀል ተግባራት በተለይም በብሔር ወይም በክልሎች መካካል በግለሰቦችና ቡድኖች በሚፈጠር ግጭት መነሻነት ወንጀል የተፈጸመባቸው አካባቢዎች ዋና ዋና ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ በማድረግ የተደራጀ የምርመራና ክስ የመመስረት ሂደት ላይ እንገኛለን።
በዚህ መሰረት፣ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ጉጂ ዞን እና በደቡብ ክልል ጌደኦ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች፣ በሶማሌ ብሔራዊ ክልል በጅግጅጋና ሌሎች ዞኖች፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል ካማሽ ዞን፣ መተከል ዞን፣ በደቡብ ክልል በሀዋሳ፣ በቴፒና ሸካ ዞን፣ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ አርሲ፣ ምሰራቅ ሀረርጌ፣ ባሌ ዞን፣ ምዕራብ አርሲ፣ ምዕራብ ሸዋ እና አዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር፣ በአዊ ብሄረሰብ ዞን በጃዊ ወረዳ፣ በጎንደር፣ በአዲስ አበባ በሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም በአንዳንድ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተፈጸመውን ወንጀል ድርጊቶችን መነሻ በማድረግ ተጠሪጣሪዎችን ቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ ተጀምሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የካቲት 5 ቀን 2012 ዓ.ም በክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ የፌደራል የፍትህና የጸጥታ መዋቅር አመራሮች እንዲሁም የክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮችና የፍትህና የጸጥታ መዋቅር አመራሮች ባካሄዱት አስቸኳይ ግምገማ ለውጡን ተከትሎ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ማንነትን መሰረት ያደረጉ፣ በሃይማኖት ተቋማት ላይ እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች እንዲሁም በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ ለማቅረብ ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት ህዝቡን ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
መንግስት በለውጡ ማግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በህግና ፍትህ ስርዓቱ ላይ እምርታዊ ለዉጥ ለማምጣት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን እንደነበረ እሙን ነው። የፍርድ ወሳኔ ያገኙና ጉዳያቸው በምርመራ ላይ ያሉ ተጥርጣሪዎችን በምህረት አዋጅ ክሳቸው እንድቋረጥ ተደርጓል። በርካቶቹ በይቅርታ ከእስር እንዲፈቱ ተደርገዋል። ይህ የመንግስት ሆደ ሰፊነትን ያልተረዱ አንዳንድ አካላት ኢ-መደበኛ በሆነ ቡድናዊ አደረጃጀት በርካታ ወንጀሎችን ሲፈጽሙ ተሰተውሏል። በዚህም ክቡር የሰው ልጅ ህይወት ጠፍቷል፣ የህዝብና የመንግስት ሀብትና ንብረት ተዘርፏል፣ ወድሟል። ስለሆነም ከእንግዲህ ወዲህ ለሀገራችን ደህንነትና ለህዝባችን ህልውና ሲባል ከዚህ በኋላ ማናቸውንም በወንጀል ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ አካላትን እንደማይታገስ ጽኑ አቋም ተይዟል። ከፍተኛ አመራሩ ባደረገዉ ግምገማ በየቦታው የሚፈጠሩ የወንጀል ድርጊቶች ዋነኛ ችግር የፖለቲካ አመራሮች እጅ ያለበት መሆኑን በሚገባ የተረዳ ሲሆን፥ ይህን የማይገባ ተግባር ሲያስፈጽም እና ሲፈፅም በዝምታ ሲያልፍ የነበረው አመራር ከዚህ እንዲታረም በዚህ አጋጣሚ ማሳሰብ ይፈልጋል።
በሀገሪቱ በሚፈለገው መጠን የህግ የበላይነትን በማስከበር ዘንድ የነበረውን ፈተና ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የምንሻገረው እንደሚሆን እሙን ነው። ስለሆነም ይህን ህገ ወጥ ተግባራትን የምንሸከምበት ጫንቃ እና በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለፍርድ የማናቀረብበት ምንም ምክንያት የማይኖረን መሆኑን እንገልጻለን። ስለሆነም በዛሬው መድረካችን በተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ የተሳተፉ አካላትን በህግ ፊት ለማቅረብ፣ የዜጎች ሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመከላከል የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲሁም ተጠርጣሪዎች በህግ ፊት እንዲቀርቡ በሚደረገዉ ጥረት ላይ የሚያደናቅፉ አካላት ላይ ያለምንም ምህረት በማያዳግም ሁኔታ ተጠያቂ የሚያደረግ መሆኑን መግለጽ ይፈልጋል።
በሌላ በኩል ከወንጀል ድርጊቶች ጋር በተያያዘ የተጀመረው የተጠረጠሩትን ግለሰቦች ለፍርድ የማቅረብ ሂደቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፤ በዚህም የህግ የበላይነትን የማስከበር እንቅስቃሴ ለድርድር አይቀረብም። ህብረተሰቡም ጥፋት ፈፃሚዎችን ለህግ ለማቅረብ በሚደረገው ርብርብ እንደ ወትሮው ሁሉ አሁንም የተለመደ ትብብሩን እንዲቀጥል በዚህ አጋጣሚ እንጠይቃለን።
ኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የካቲት 5 ቀን 2012 ዓ.ም አዲስ አበባ