አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዱባይ ከኢትዮጵያውያን ጋር የሚያደርጉት ውይይት በቀጣይ ኢትዮጵያ በመካከለኛው ምስራቅ የምትከተለውን የስራ ስምሪት አቅጣጫ ለመወሰን እንደሚረዳ በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው እለት ወደ ተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ያቀኑ ሲሆን፥ በቆይታቸውም በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን መብት እና ጥቅም የሚያስከብሩ ውይይቶችን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
አምባሳደር ሱሌይማን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በስልክ ባደረጉት ቆይታ፥ በዛሬው እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይን ለመቀበል ዝግጅቱ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
በነገው እለት በዱባይ ስታዲየም ታላቅ መድረክ ይካሄዳል ያሉ ሲሆን፥ በነገው መድረክ ላይም ቁጥራቸው እስከ 15 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
በመድረኩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ፊት ለፊት የመገናኘትን እድል እንደሚፈጥርም አምባሳደር ሱሌይማን ተናግረዋል።
በማግስቱ ቅዳሜ ሴቶች ብቻ የሚሳተፉበት መድረክ እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል።
በሪያድ የስልጤ ማህብረሰብ የስራ አመራር ቦርድ አባል እና በሪያድ የህዳሴ ግድብ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ኑሪ ኢስማኤል፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የዱባይ ጉብኝት ካለው ጠቀሜታ አንጻር ደስታን እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት አድርገው የተለያዩ ውሳኔዎችን ማስቀመጣቸው ይታወሳል።
በስላባት ማናዬ