አዲስ አበባ፣ ህዳር 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህልውና ዘመቻው መዳረሻ አሸባሪው ህወሓት ዳግም የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ፈተና እንዳይሆን ማድረግ ነው ሲል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ አስታወቀ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ዛሬ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የጸጥታ ኃይሎች የጋራ ጥምረት እያካሄደ ባለው “ ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” ወደ ተወረሩት አካባቢዎች በጥልቀት በመግባት፣ አሸባሪው ህወሓት ትጥቁን፣ ስንቁን፣ ኃይሉንና ጀሌውን እንዲሁም የዘረፈው ንብረት ይዞ እንዳይወጣ እያደረገው እጅ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነውንም እየደመሰሰው ይገኛል ብሏል።
የዕዙ ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የጸጥታ ኃይሎች የጋራ ጥምረት በሚያካሄዱት ‹ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት› ወደ ተወረሩት አካባቢዎች በጥልቀት በመግባት፣ አሸባሪው ሕወሐት ትጥቁን፣ ስንቁን፣ ኃይሉንና ጀሌውን እንዲሁም የዘረፈው ንብረት ይዞ እንዳይወጣ እያደረገ ይገኛል፡፡ እጅ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነውንም እየደመሰሰው ይገኛል፡፡
ባለፉት ሁለት ተከታታይ ቀናት በተደረገው ኦፐሬሽን በሸዋ ግንባር የቀወት ወረዳ፣ ለምለም አምባ፣ ጀውሐ፣ ሰንበቴ፣ አጣየ እና ካራ ቆሬ ከተሞችና አካባቢዎች ከወራሪው ኃይል ነጻ ወጥተዋል፡፡ በጋሸና ግንባር ደግሞ ኮን እና ዳውንት ሙሉ በሙሉ ከአሸባሪው ጸድተዋል፡፡ በወረኢሉ ግንባር ልጓማ ከተማ ነጻ ወጥታለች፡፡ በተወረሩት አካባቢዎች የጸጥታ ኃይሎች የጋራ ጥምረት ባካሄዱት ኦፐሬሽን በሺዎች የሚቆጠሩ የአሸባሪው ሕወሐት ጀሌዎች እጃቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
የየአካባቢው የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ በየጢሻው የገባውን የአሸባሪ የሕወሐት ጀሌ እጁን በሰላም እንዲሰጥ እያደረጋችሁ ያላችሁትን ጥረት አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ መንግሥት ያሳስባል፡፡ ኅብረተሰቡም በየአካባቢው የተበተነውን የአሸባሪው የሕወሐት ጀሌ ተደራጅቶ በመማረክ፣ የነፍስ ወከፍ መሣሪያውን እንዲታጠቅ፣ የቡድንና ሌሎች መሣሪያዎችን ደግሞ ለጸጥታ አካላት እንዲያስረክብ በድጋሚ ጥሪ ቀርቦለታል፡፡ ምርኮኛን መከባከብ የጀግንነት ባህላችን
አንድ አካል በመሆኑ ማኅበረሰቡ ምርኮኞችን ለጸጥታ አካላት እንዲያስረክብ መንግሥት ጥሪ ያደርጋል፡፡
አሸባሪው ሕወሐት እየተሸነፈ በመሆኑ በግንባር ያጣውን ድል በሐሰት መረጃ ለመሸፈን እየጣረ ነው፡፡ አሸባሪው ሕወሐት የኢትዮጵያ ልጆችን ብርቱ ክንድ መቋቋም አቅቶት ሲፍረከረክ፣ የአሸባሪው አመራሮች መሸነፋቸውን ላለማመንና ወጣቶችን ውጤት በሌለው ጦርነት አሁንም ለመማገድ በማሰብ፣ ስልታዊ ማፈግፈግ አድርገናል በማለት ራሱንና ተስፈኛ ጋላቢዎቹን በማጽናናት ላይ ይገኛል፡፡ አሸባሪው ሕወሐት ከዚህ በኋላ ለወረራ የገቡ ጀሌዎቹን የሚያድንበት ዐቅም የለውም፡፡ ወደተወረሩ አካባቢዎች የገባው የአሸባሪው ሕወሐት ጀሌ ሁሉም የመውጫ በሮች ተዘግተውበታል፡፡ በመሆኑም ወራሪው ኃይል በከንቱ ያሰለፋችሁ ወጣቶች ከዚህ በኋላ ማምለጫ እንደሌላችሁ ተገንዝባችሁ፣ እጃችሁን ለጸጥታ አካላት በመስጠት፣ ራሳችሁን እንድታድኑ መንግሥት ያሳስባል፡፡
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት ነጻ ያልወጡ አካባቢዎችን በተሟላ መልኩ ነጻ ለማውጣት በተጋድሎ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ሁላችን ተባብረን አሸባሪው ኃይል ዳግም የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ፈተና እንዳይሆን ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የመከላከያ ኃይላችንን በሰው ኃይል፣ በአደረጃጀትና በትጥቅ ዐቅም አጠናክረን በማንኛውም ወገን የሚታፈርና የሚከበር መከላከያ ኃይል መገንባት ይገባናል፡፡ መከላከያ ኃይላችንን በተሻለ ሁኔታ ለመገንባትም ሕዝቡ የጸጥታ አካላትን ለመደገፍ የጀመረውን ርብርብ ከበፊቱ በተሻለ መንገድ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ወጣቶችም የመከላከያ ሠራዊቱን በብዛትና በዓይነት በመቀላቀል ሀገራቸው መቼምና በማንም የማትደፈር እንዲያደርጉ ታሪካዊ አደራ አለባቸው፡፡
አሸባሪው ሕወሐት ለሰው ልጅ ኑሮና ለሰብአዊ መብት የማይጨነቅ፤ የዕድገትና ለሥልጣኔ ፀር የሆነ እኩይ ኃይል መሆኑን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በገሐድ አሳይቷል፡፡ ማኅበራዊ ተቋማትን አፈራርሶና አውድሞ፣ የግለሰቦችን ንብረት ዘርፎና አጥፍቶ፣ የየአካባቢውን ነዋሪዎች ረሽኖ፣ ሴቶችን ደፍሮና በሕጻናት ላይ አሰቃቂ ጉዳት አድርሶ በሰው ልጅ ላይ ተፈጽሞ የማያውቅ ከባድ ወንጀል ፈጽሟል፡፡ የሃይማኖት ቦታዎችን አርክሷል፤ አውድሟል፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን አቃጥሏል፡፡ ታሪካዊ ቦታዎችንና ቅርሶችን አፈራርሷል፡፡ ለዚህም ነው አሸባሪው ሕወሐት የትግራይን ሕዝብ አይወክልም የምንለው፡፡ በመሆኑም ይሄን የአሸባሪው ሕወሐት የጥፋት ተግባር ለሰዎች መብት የሚታገሉ ሁሉ ሊያወግዙት ይገባል፡፡ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የህልውና ዘመቻው መዳረሻ አሸባሪው ሕወሐት ዳግም የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ፈተና እንዳይሆን ማድረግ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ኅብረተሰቡ የጀመረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ እስከመጨረሻው አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡
ድላችንን የምናስከብረው በተባበረ ክንዳችን ነው፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ