አዲስ አበባ ፣ የካቲት 5 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በናይጄሪያ በላሳ ትኩሳት ወረርሽኝ የሟቾች ቁጥር ወደ 70 ከፍ ማለቱ ተነገረ።
በወረርሽኙ ተይዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰወች ቁጥር ደግሞ ከ700 ወደ 1 ሺህ 708 ከፍ ማለቱ ተነግሯል።
የናይጄሪያ የበሽታ መቆጣጠር ማዕከል ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በሦስት ግዛቶች በላሳ ትኩሳት ስምንት ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል።
በወረርሽኙ የተጠቁት ሰወች ቁጥርም 472 መድረሱንም ነው ማዕከሉ የገለጸው።
ከዚህ ባለፈም በሶስት ግዛቶች አራት የህክምና ባለሙያዎች መጠቃታቸውንም ገልጿል።
የላሳ ትኩሳት በፈረንጆቹ 1969 ለመጀመሪያ ጊዜ በተከሰተባት የናይጀሪያዋ ላሳ ከተማ ስያሜውን አግኝቷል።
እንደ አሜሪካው የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከል ማእከል ገለጻ በምዕራብ አፍሪካ በላሳ ትኩሳት በየዓመቱ ከ1 መቶ እስከ 3 መቶ ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ይጠቃሉ።
ከዚህ ውስጥ 5 ሺህ ያክሉ ለህልፈት እንደሚዳረጉም የማዕከሉ መረጃ ያመላክታል።
ከዚህ ቀደም የላሳ ትኩሳት በሴራሊዮን፣ ላይቤሪያ፣ ቶጎ እና ቤኒን መታየቱ ነው የተገለጸው።
ምንጨ፦ አልጀዚራ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision