Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ምክር ቤቱ የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን በተመለከተ የቀረበ አዋጅን አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበ አዋጅን አፀደቀ።

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሄደ።

ምክር ቤቱ በዛሬው አስቸኳይ ስብሰባው የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ተመልክቷል።

አዋጁ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ለማህበራዊ ስምሪት፣ ለፖለቲካ መረጋጋት፣ ለሀገራዊ አንድነት፣ ለሰብዓዊ ክብር እና ለብዝሃነት ጠንቅ መሆኑን በመገንዘብ በተለይም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በህብረተሰቡ መካከል ያሉ መልካም እሴቶች በጥላቻ ንግግሮችና በሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ እየተሸረሸሩና ለሀገርም ስጋት እየደቀኑ በመሆናቸው እንዲሁም እነዚህን ችግሮች አሁን ባሉት ህጎች መፍታት የማይቻል በመሆኑ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

የጥላቻ ንግግር እና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ዴሞክራሲያዊ ውይይት እና ክርክር ለማድረግ እንቅፋት በመሆኑ ከብሄር እና ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ የጥላቻ ንግግር እና ሃሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨትን እንዲሁም ዘርን፣ ጾታን እና አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ የሚደረጉ የጥላቻ ንግግሮች እና ሃሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም ተገልጿል።

እንዲሁም የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭትን በህግ መከልከል አስፈላጊ በመሆኑ የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱም ተነግሯል።

የምክር ቤቱ አባላትም በአዋጁ ላይ ያላቸውን ሃሳብ እና አስተያየት የገለጹ ሲሆን፥ ለአብነትም ይህ አዋጅ የዜጎችን ሃሳብ በነጻነት የመግለጽ መብት የሚጋፋ እንደሆነ ያነሱ ሲሆን፥ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥቶበታል።

በዚህም አዋጁ በህገ-መንግስቱ ላይ ከተቀመጠው የመናገር መብት ጋር እንደማይቃረን፣ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 29 (6) እና (7) ከተቀመጡት ገደቦች ውስጥም አንዱ ምክንያት ሰብአዊ ክብርን መጠበቅ ሲሆን፥ የጥላቻ ንግግር ሰብአዊ ክብርን የሚነካ ዋነኛው በመሆኑ ከተቀመጠው ገደብ ጋር የሚገናኝ መሆኑ ምላሽ ተሰጥቶበታል።

ምክር ቤቱ የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበ አዋጅን በ23 ተቃውሞ እና በ2 ድምጸ ተአቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።

በሙለታ መንገሻ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

Exit mobile version