የሀገር ውስጥ ዜና

አንጋፋው አርቲስት ጀምበሬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

By Tibebu Kebede

February 13, 2020

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በመድረክ ትወና ከ40 ዓመታት በላይ ያገለገሉት አንጋፋው አርቲስት ጀምበሬ በላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

አርቲስቱ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1949 እስከ 1953 ዓ.ም በቀድሞዉ የሀገር ፍቅር ማህበር በአሁኑ የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በመድረክ ትወና አገልግለዋል።

እንዲሁም ከ1953 እስከ 1988 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በመድረክ ትወና ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

አርቲስት ጀምበሬ ከተወኑባቸዉ ሥራዎች መካካል የአዛውንቶች ክበብ፣ ኦቴሎ፣ የከተማዉ ባላገር፣ ሐምሌት፣ የዋናው ተቆጣጣሪ፣ የእጮኛዉ ሚዜ፣ የልብ ፅጌሬዳ፣ 1 ዓመት ከ1 ቀን፣ የፌዝ ዶክተር፣ የእግር እሳት፣ የሚስጢር ዘብ እና የድል አጥቢያ ጥቂቶቹ ናቸው።

በተጨማሪም የዘመቻው ጥሪ፣ አመል አለብኝ፣ ግራ የገባው ግራ፣ ያልተከፈለው እዳ የተሰኙ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ መተወናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አርቲስት ጀምበሬ በላይ በ1933 ዓ.ም በቀድሞው ጎጃም ክፍለ ሀገር የተወለዱ ሲሆን፣ የሁለት ሴት እና የአራት ወንድ ልጆች አባት ነበሩ።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision