Fana: At a Speed of Life!

16 የመንግስትና የግል ተቋማት የኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 16 የመንግስትና የግል መስሪያ ቤቶች የኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ በዛሬው እለት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱንም የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ መረጃና መረብ ደህንነት ኤጄንሲ ጨምሮ በአጠቃላይ 16 የግልና የመንግስት ተቋማት ተፈራርመዋል።

በስካይ ላይት ሆቴል በተደረገው የፊርማ ስነ ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፥ የኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎት ያደጉ ሀገራትና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ለንግድ ተወዳዳሪነት የሚጠቀሙበት አገልግሎት መሆኑን አንስተዉ ንግድን ለማሳለጥና ቀልጣፋ አግልግሎት ለመስጠት ያግዛል ብለዋል፡፡

አገልግሎቱ በሀገሪቱ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ቀላል፣ ተገማች፣ ቀልጣፋና ፈጣን ያደርገዋል ብለዋል።

ይህ ፕሮጀክትም ቅድመ ዝግጅት ስራዉን አጠናቆ ወደ ትገበራ ለመግባት ሊደርስ የቻለዉ በለውጡ በቁርጠኝነት በማናበብና በመቀናጀት በጋራ በመሰራቱ ስለሆነ ለቀጣይ ስራዎችም በአብሮነትና በቅንጅት ከሰራን ስኬታማ መሆን እንደምንችል ያሳየ ነው ብለዋል።

አሰራሮችን ወረቀት አልባ በማድረግ ቀላል አለም አቀፍ የንግድ ስርዓትና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጠው ይህ ስርዓት አገራዊ ገቢን በማሳደግ፤ ወጪን የሚቆጥብና የአገልግሎት አሰጣጥ ግዜን የሚቀንስ በመሆኑ ወደ ተግባር ሲገባም ዛሬ የተፈረመውን ዉል በአግባቡ በመከወን ስኬታማ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

አሰራሩ ሙስናን በመቀነስ የደንበኞች እርካታን ይጨምራል፤ አለም አቀፍ ንግድን በማበረታታት ግልፅነትን ያሰፍናል መባሉንም ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.